ኢትዮጵያና የጦርነቶች ታሪኳ

Wednesday, 28 February 2018 12:22

 

በጥበቡ በለጠ

 

ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የምትጠቀሰው በተለያዩ ጊዜያት በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ በሚከሰቱ ጦርነቶች የእርስ በርስ ግጭቶች አማካይነት ነው። ኢትዮጵያ ነፃነቷንና ክብሯን ጠብቃ የጥቁር ዓለም ሕዝብ ሁሉ ምሳሌ ለመሆን የበቃችው በየጊዜው ከሚከሰቱባት ወራሪዎች፣ ቅኝ ገዢዎችና አስገባሪዎች መዳፍ ሥር ላለመግባት ዜጐቿ በየዘመናቱ በከፈሉት መስዋዕትነት አማካይነት ነው።


ከዚሁ ባልተናነሰ እና ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ የሀገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነቶች ደግሞ የትየለሌ ሆነው ኖረዋል። ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ብትሆንም፤ መሪዎቿ በየጊዜው በሚቀያየሩባት ወቅት ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ባለመኖሩ ምክንያት የዜጐቿ ሕይወት ክፉኛ እየተቀጠፈ መሪዎች ይቀያየራሉ።


ከኋለኛው ዘመን ተነስተን ዘመናችንን ብንቃኝ ኢትዮጵያ በሰላምና በመረጋጋት የቆየችባቸው ዓመታት ጥቂቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።


በአክሱም የነበረው የኢትዮጵያን ሥልጣኔ እየተዳከመ ሄዶ የወደቀው በጦርነት ምክንያት ነው። ታሪኳ እስካሁን በሥርዓት ያልተፃፈላት ዮዲት ጉዲት ተነስታ ብዙ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ማማዎች እንዳፈራረሰች ይነገራል። ዮዲት ማን ናት? ለምን እንዲህ አይነት ጥፋት ውስጥ ገባች? ሰዎች ጥፋት ውስጥ እንዳይገቡ ምን ማድረግ አለብን በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ቀጣዮቹ መሪዎች ተወያይተው ማስተካከያ ባለማድረጋቸው ግጭቶች እየተተኩ ይመጣሉ።


በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥልጣን ወደ ዛጉዌ አስተዳደር ከሄደ በኋላ በአክሱም፣ በቀይ ባህር እና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የነበሩት ስልጣኔዎችና ግንኙነቶች እንደ ቀድሞው አልሆኑም። የዛጉዌ ስርወ መንግሥት የራሱ የሆኑ የሥልጣኔ ልዩ መገለጫዎች ቢኖሩትም ቀደም ብሎ ከታየው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ጋር አብሮ ተሰናስሎ መሄድ አልቻለም። አንዱ ሲከስም ሌላው ብቅ ይላል እንጂ፣ በነበረው ሥልጣኔ ላይ ተዳምሮ የሚዘልቅ የኢትዮጵያ እድገት አልታይ ካለ የረጅም ጊዜ ታሪኩ ነው።


የዛጉዌ ሥርወ መንግስት ለ300 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመራ፣ በሌሎቹ ሰለሞናዊያን የነገስታት ሐረግ ደግሞ ሥርዓቱን ለመጣል ትግል የሚደረግበት ነበር። 300 ዓመታት ሰለሞናዊያን በዛጉዌዎች ተነጠቅን የሚሉትን ሥልጣን ለመመለስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትግል የሚካሄድበት ወቅት ነበር። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ቢኖር ኖሮ ዛጉዌዎች ያሳዩት ሥልጣኔ ብዙ እጥፍ ሆኖ ያድግ ነበር። በነዚህ ግጭቶች መካከል ኢትዮጵያን ሊያሳድጋት የሚችለው ዕድል የመከነበት ወቅት ነው።


በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥልጣን ወደ ሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ቢሸጋገርም፤ የውስጥ የርስ በርስ ግጭቶች አሁንም አልቆሙም። ነገስታት በየጊዜው ጦርነት ስለሚያደርጉ ዋና ከተማቸውን አንዱ ከተማ ላይ ተረጋግተው መመስረት አልቻሉም ነበር። የተረጋጋ ኑሮ ስለሌላቸው ከቦታ ቦታ እየሄዱ ድንኳናቸውን እየደኮኑ መኖር ነበር ስራቸው። አንዱ ሌላውን ጥሎ ሲያሸንፍ ሌላ ቦታ መናገሻውን ይመሠርታል። በዚህ ሳቢያ ተረጋግቶ፣ ዋና ከተማ መስርቶ፣ የትምህርት ተቋማትን መገንባት፣ የጥናትና የምርምር ማዕከላትን መመስረት አልታይ ብሎ ነው በኢትዮጵያ ምድር የዘገየው። ታዲያ በአነዚህ ዘመናት ውስጥ አውሮፓውያን የዕድገትን ካብ በየከተሞቻቸው እየገነቡ ቆይተዋል።


16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ስንመጣ፣ ኢትዮጵያ እጅግ አስቸጋሪ ውጥንቅጥ ውስጥ የገባችበት ወቅት ነበር። 15 ዓመታት ሙሉ ከምስራቅ ኢትዮጵያ የተነሳ ጦርነት እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ድረስ ብዙ ሀብትና ንብረት እንዲሁም የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት እየቀጠፈ ተጉዟል። ኢትዮጵያ እጅግ የፈረሰችበት መጥፎ ታሪኳ ነው። ከውጭውም ቢሆን እንደ ኦቶማን ቱርኮች የቀይ ባህር መተላለፊያ ላይ ተገማሽረው ኢትዮጵያ ላይ ሲያሴሩና ተፅዕኖ ሲፈጥሩ መቆየታቸው በታሪክ ውስጥ ተፅፎ ይገኛል። ይህን የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጦርነት ሃይማኖታዊ ገፅታ እንዲኖረው የኦቶማን ቱርኮች፣ የፖርቹጋሎችና የስፓንያርዶች እጅ ጐልቶ ታይቶበታል። እነዚህ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው ውጣ ውረዶች የተከሰቱበት ዘመን ነበር።


የኢትዮጵያ መናገሻነት ከሸዋ ተነስቶ ወደ ሰሜን ጐንደር አመራ። የፖርቹጋሎችና የስፓንያርዶች ተፅዕኖ እያየለ ጐንደር ዙሪያ መናገሻ እንደሆነች ቀጠለች። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የሃይማኖት ግጭት ተነስቶ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያንም አለቁ። በ1624 ዓ.ም አፄ ፋሲል ወደ ሥልጣን ሲመጡ ብዙ የደም ዋጋ የተከፈለበት ዘመን ነበር። ከእርሳቸው በኋላም ለ200 ዓመታት ጐንደር ዋና ከተማ በመሆን ረጅም ጊዜ አስቆጠረች። አንፃራዊ ሠላምም ታየ። እንደገና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወደ ግጭቶች ማዕበል ገባች።


19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓ ወደ ኢንደስትሪው ዓለም ሲሸጋገር ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ጦርነት፣ መከፋፈል እና የእርስ በርስ ግጭቶች ገባች። በየቦታው ተከፋፈለች። አንድነቷ እየተመናመነ መጣ። ልዩ ልዩ አፄዎች መጡ። አንዱ ሌላው ላይ የበላይ ለመሆን በሚያደርገው ጦርነት ኢትዮጵያ ደቀቀች።


ይህን የኢትዮጵያ መከፋፈልን አንድ አደርጋለሁ በማለት አፄ ቴዎድሮስ ተነሱ። እርሳቸውም እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከልዩ ልዩ ግዛተ-አፄዎች ግር ተዋጉ። በዚህ ረጅም ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያ እጅግ እየተጐዳች ሄደች። አፄ ቴዎድሮስ ጦርነቱን አጠናቀው አንዲት ኢትዮጵያን እገነባለሁ ብለው ባለሙ ጊዜ ደግሞ ከእንግሊዞች ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ። የእንግሊዝ ጦር በጀነራል ናፒር እየተመራ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገባ። ያንን ሁሉ የሀገር ውስጥ ጦርነት አካሂደው የመጡት አፄ ቴዎድሮስ እንደገና ከእንግሊዞች ጋር ውጊያ ተጀመረ። እርሳቸውም ሠራዊታቸውን በተኑ። ራሳቸውም ህይወታቸውን ሰው። ኢትዮጵያ አሁንም ችግር ውስጥ ገባች። መንግስት አልባ፣ ወደ እርስ በርስ ግጭቶች የሚያመራ አደጋ ተጋረጠባት።


ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ተገላገለችና አፄ ዮሐንስ ወደ መንበረ ስልጣኑ መጡ። የእርሳቸውም ዘመን ጦርነቱ በተለይም ከደርቡሾች ጋር ተደረገ። አፄ ዮሐንስ ሀገራቸውን ለማዘመንና ለማሳደግ የነበራቸው ህልም በጦርነቱ ምክንያት አልተሳካም። ጦርነቱ አይሎ አፄ ዮሐንስ የራሳቸውን ህይወት አጡባት። ጭራሽ ደርቡሾች አንገታቸውን አስከመቁረጥ ደርሰዋል። መሪዎቿ አንገታቸውን እየሰጡላት በጦርነት ውስጥ የኖረች አገር ናት ኢትዮጵያ።


ከዚህም መስዋዕትነት በኋላ ሥልጣን ወደ አፄ ምኒልክ ቢመጣም ጣሊያኖች በ1888 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረሩ። የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ ድል እስከሚገኝ ድረስ እድገት፣ ሥልጣኔ፣ ትምህርት፣ ምርምር የሚባል ነገር አልነበረም። ጦርነቱ ረሀብ አስከትሏል። ከጦርነቱ መልስም ወደ መደበኛ የሀገር አመራር ለመምጣት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ።


የአፄ ምኒልክ ዘመን ላይ መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር ወድቆ፣ ኢትዮጵያም በቅኝ ገዢዎች ተከባ ችግር ውስጥ ነበረች። ቅኝ ገዢዎቹ ዙሪያዋን ይዘዋት ነፃ አገር ሆና የምትፈልገው እድገትና ግስጋሴ ሳትደርስ ያም ዘመን አለፈ።
ከአፄ ምኒልክ በኋላም የሥልጣን ሽኩቻው አይሎ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተካሄዱ። አሁንም ኢትዮጵያ ተዳከመች።


አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከ5 ዓመታት በኋላም ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። ፋሽስቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት አመታት በቆዩበት ወቅት እነዚያ አመታት በሙሉ የታላቅ ጦርነት ወቅቶች ነበሩ።


የአምስቱ ዓመታት ጦርነት ካለቀ በኋላም ሀገርን አረጋግቶ ማሳደግ መምራት በራሱ ብዙ ውጣ ውረድ ያለው ነበር። እንደገናም የእርስ በርስ ጦርነቱ እና አልፎ አልፎም ቢሆን የውጭው ተፅዕኖ እንደገና መምጣት ጀመረ። ከኤርትራ ጋር የነበረው ግጭትም ከዚያ ዘመን አንስቶ ለ30 ዓመታት መጓዝ ጀመረ።


የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ለመለወጥ በ1953 ዓ.ም የነጀነራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መጣ። እሱን ተከትሎ በርካታ ታላላቅ ሰዎች አለቁ።


ችግሩ ቀጠለ። አዲስ የአብዮት ጅምር መቀጣጠል ጀመረ። የመሬት ላራሹ ጥያቄ መጣ። ወጣቱ አብዮት አቀጣጠለ። ተቃውሞዎቹ በየቦታው መለኮስ ጀመሩ። እንቅስቃሴው እያየለ ሲመጣ ወታደሮች የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት አፍርሰው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግን መሠረቱ። ከ60 በላይ የሀገር መሪዎችን ሕይወት በጅምላ አጠፉ። ከዚያም ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የሚባሉ ቡድኖች ለግድያ ተደራጅተው ኢትዮጵያዊያኖች አለቁ። የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን ወርሮ ብዙ ሺህ ዜጐች አልቀዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት ያህል ጦርነቶች ተደርገዋል።


ዘመነ ደርግ ጦርነት የበዛበት ብዙ ምስቅልቅል የመጣበትና መረጋጋት ጠፍቶ ስደት፣ ረሀብ፣ ድርቅ መለያ የሆነበት ታሪክ ነው። ያ ሁሉ ችግር አልፎ በ1983 ዓ.ም አዲስ ሥርዓት መጣ። ተቃዋሚ የሚባሉ ኃይላት በሙሉ ተሰባስበው ሕገ-መንግስት ጽፈው አዲስ ሥርዓት መሠረቱ። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንቢያው ዘመን መምጣቱ ሲነገር ቆይቷል። የዴሞክራሲ መገለጫ የሆኑት የካርድ ምርጫ፣ የሚዲያ ነፃነት፣ የመናገር የመሰብሰብ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመደራጀት ሌሎችም መብቶች መፈቀዳቸው ተጽፏል። እንዲህ አይነት የዴሞክራሲ መገለጫዎችን በየጊዜው ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ብዙዎች ይስማሙባቸዋል። ከሕቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያን ወደ ተለመደው የግጨቶች ታሪክ የሚመሩ አዝማሚያዎች ይታያሉ። የግጭት የጦርነት መብዛት ኢትዮጵያን አሳድጐ የምናልማት ሀገርን እንዳናገኝ አድርጐናል። ስለዚህ እነዚህን የታሪክ ሂደቶቻችንን በደንብ በመመርመር ሥርዓቱ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሀገራችን ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ በመውደድ በሰላም፣ በመዋደድና በመቻቻል እናቆያት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
13010 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 725 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us