አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ሥራውን በይፋ ጀመረ

Thursday, 13 July 2017 14:20

 

በድንበሩ ስዩም

      የኢዲ ስቴላር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ የሆነው አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ከትናንት በስቲያ ሐምሌ ሶስት ቀን 2009 ዓ.ም በተለምዶ ሲ. ኤም ሲ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ሕንፃ ላይ አያሌ ታዳሚያን በተገኙበት ሥነ- ሥርዓት የሬዲዮ ጣቢያውን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ የሰጡት የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ መስራችና ባለቤት አቶ እሸቱ በላይ፣ የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እና የሬዲዮ ጣቢያው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ካሳ አያሌው ካሣ ናቸው።

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የጣቢያው አመራሮች እንደገለፁት አሐዱ ሬዲዮ በዋናነት የሚሰራባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች አስረድተዋል። ከነዚህ መካከልም ሬዲዮ ጣቢያው በየሰዓቱ ዜና የሚያቀርብ ሲሆን ስርጭቱም ለ24 ሰዓታት የማይቋረጥ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የገለፁት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪኮች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ አስተሣሰቦች፣ ፖለቲካዊ አመለካከቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ጉዳዬ ብሎ የያዛቸው ስራዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ጉዳዮችንም ወደ ኢትዮጵያ ሲተረጎሙ አንዳች ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

ኃላፊዎቹ በእጅጉ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩበት ጉዳይ ሬዲዮ ጣቢያው የሚሠራው ለኢትዮጵያዊያን ስለሆነ “የኢትዮጵያዊያን ድምጽ” ብለውታል። ኢትዮጵያ ያለፈ ታሪኳ፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና የወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሬዲዮ ጣቢያ ነው ተብሏል።

ከታዳሚያን የተነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎቸም በዕለቱ ተነስተዋል። የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ኤዲቶሪያል ፖሊሲን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ፣ አሐዱ ሬዲዮ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ሕግን፣ የሀገሪቱን ልዩ ልዩ ህጎችና ደንቦች በማክበር፣ አለማቀፍ ስምምነቶችን እና የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርን መሠረት አድርጎ የተሰናዳ መመሪያ እንዳላቸው አውስተዋል።

ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ከተሰጠ በኋላም የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ 94.3 FM አደረጃጀቱ ምን እንደሚመስል ጉብኝት ተደርጓል። ሬዲዮ ጣቢያው እጅግ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑ ይፋ ሆኗል። አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ከበርካታ ተባባሪ አካላት ጋርም እንደሚሰራ ተነግሯል። በዕለቱ በፅሁፍ የቀረበው ጋዜጣዊ መግለጫም የሚከተለውን ይመስላል።

አሐዱ ሬዲዮ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ በተሰማራው እና የኢዲ ስቴላር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ በሆነው ኢዲ ስቴላር ሚዲያ ሴንተር የተቋቋመ፣ ዘርፈ ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ነው።

ኢዲ ስቴላር ባለፉት 20 ዓመታት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገሮች በልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተሰማርቶ ካከናወናቸው ሥራዎች ጎን ለጎን፣ ታላላቅ የአደባባይ ላይ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ከጅምሩ እንደ ህልም ይዞ ሲንቀሳቀስበት የቆየውን የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን የመክፈት ዕቅዱን ለማሳካት መንገዱን ሲያመቻች ቆይቷል። ዋነኛ ሥራዎቹንም ከሕዝብ ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ በማሰብ ታላላቅ የንግድ ትርዒቶችን አካሂዷል፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ ታላላቅ ኢቨንቶችን አስተባብሯል፤ ከአስር ዓመት በላይ የሬዲዮ ፕሮግራም በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ አዘጋጅቶ ሲያቀርብም ቆይቷል፤ በየተወሰነ ጊዜ የሚወጣ መጽሔትም አሳትሟል።

“አውቶሞቲቭ ጆርናል” የሬዲዮ ፕሮግራም፣ አውቶ ፕላስ” መጽሔት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ በዐይነቱ የመጀመሪያ እና ብቸኛ የሆነውናኢንተርናሽናል አውቶሞቲቭ ፌር” የተባለው ዓለማቀፍ የንግድ ትርዒት፤ በየጊዜው የሚያስተባብራቸው አውደ ጥናቶች፣ ታላላቅ ጉባዔዎች እና ሌሎችም የመድረክ ዝግጅቶች ኢዲ ስቴላር የመገናኛ ብዙኃንን ሥራ ባህሉ አድርጎ ለመቆየቱም ምስክሮች እና ለአሐዱ ሬዲዮ 94.3 ኤፍ ኤም መንገድ ጠራጊዎች ናቸው። ኢዲ ስቴላር የብሮድካስቲንግ ፈቃድ ያገኘው ዘንድሮ ቢሆንም፣ ለስምንት ዓመታት ያህል የንግድ ሬዲዮ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

“አሐዱ” በግእዝ ቋንቋ “ቀዳሚ፣ የመጀመሪያ“ የሚል ትርጉም አለው፤ አሐዱ ሬዲዮም እንደ ስሙ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ፣ እና በአቀራረብ ራሱ ቀድሞ፣ አድማጮቹን ቀዳሚ ለማድረግ የሚተጋ የሬዲዮ ጣቢያ ነው።

አሐዱ ሬዲዮ፣ ምንም እንኳን የንግድ ሬዲዮ ቢሆንም፣ በመረጃ እና ዕውቀት አማካይነት፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማስታወስ እና በማስተዋወቅ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ህይወትን የማጠናከር ኃላፊነትን ወስዷል። የአሐዱ ሬዲዮ ተልዕኮ ለኢትዮጵያዊያን (እና ለመላው የሰው ልጅ) ታማኝ እና ወሳኝ የመረጃ፣ የቁም ነገር እና የመዝናኛ ምንጭ መሆን ነው።

የአሐዱ ሬዲዮ ርዕይ ደግሞ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል (Centre of Excellence) መሆን ነው።

ይህንኑ ተልዕኮውን ለመወጣት እና ርዕዩን ለማሳካት ይችል ዘንድ ጣቢያው ሶስት ጠንካራ ምሶሶዎችን አቁሟል፤ እነዚህም ሦስት ምሶሶዎች፡-

1.  በማኅበረሰቡ አኗኗር እና አስተሳሰብ ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ፣ ደጋግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲከበሩ እና ለቀና ማኅበራዊ ትስስር እንዲውሉ የሚያሳስብ፣ እውነተኛ፣ ሚዛናዊ፣ የሚጠቅም መረጃ፣

2.  ይህንን በጥንቃቄ የተሰበሰበ፣ የተተነተነ፣ እና በጥንቃቄ የተዘጋጀ መረጃ ወደ አድማጭ በላቀ የድምፅ ጥራት ማቅረብ የሚያስችል፣ ዘመኑ የደረሰባቸው የሥልጣኔ ግብዓቶች የተሟሉለት ዘመናዊ የድምፅ መቅረጫ፣ ማቀናበሪያ እና ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ፤ እንዲሁም

3.  ሐቀኛ እና ሕዝባዊ ፋይዳ ያላቸውን መረጃዎች ሰብስቦ፣ ከግራ ከቀኝ አስተንትኖ፣ በዘመናዊው የሬዲዮ ቴክኖሎጂ መረጃዎቹን አቀናብሮ አየር ላይ የሚያውል የሰለጠነ፣ በሙያው ልምድ ያካበተ፣ አዳዲስ ነገር የመፍጠር አቅም

4.  ያለው፣ ተግባብቶ በቡድን ሊሠራ የሚችል፣ እርስ በርሱ ለመማማር ዝግጁ የሆነ፣ ለሚሠራው ሙያ እና ለሚያገለግለው ሕዝብ ክብር ያለው የሰው ኃይል ናቸው።

በእነዚህ ወሳኝ ምሶሶዎች፡- በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ እና ሁለቱን አስተባብሮ ወደ አድማጭ በሚያደርሰው የሰው ኃይል አማካይነት አሐዱ ሬዲዮ፣ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሬዲዮ ሞገዱ አማካይነት፣ ሕዝቡን ከመረጃ እና ከዕውቀት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፤ የመዝናኛዎችም አመንጪም ይሆናል።

አሐዱ ሬዲዮ ዘርፈ ብዙ መገናኛ ብዙኃን ለመሆን ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ከሬዲዮው ጎን ለጎን ጠንካራ የድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን እያደራጀ ነው። ድረ ገፁ የአሐዱ ሬዲዮን መሠረታዊ ባህርያት ተከትሎ፣ ከድምፅ ባሻገር መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በፎቶ፣ እና በቪዲዮ አስደግፎ ያቀርባል፤ የሬዲዮውን ስርጭትም በኢንተርኔት አማካይነት በቀጥታ ያስተላልፋል፤ ተቀናብረው የተዘጋጁ ፖድካስቶችንም ሥርጭቱን በቀጥታ መከታተል ላልቻሉ ተከታታዮች ያጋራል። የአሐዱ ድረ ገፅ መረጃዎችን በፍጥነት ያካፍላል፣ በፍጥነት ያድሳል።

የአሐዱ የማኅበራዊ ድረ ገፅ መገናኛዎች (ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ፣ ትዊተር…) የአሐዱን የሬዲዮ እና የድረ ገፅ ተግባራት እንዲያግዙ ተደርገው ተቀርፀዋል። በእነዚህ የአሐዱ ማኅበራዊ የድረ ገፅ መገናኛዎች አማካይነት፣ መረጃዎችን፣ ምሥሎችን፣ ጥቆማዎችን የመስጠት፣ በሕዝብ አስተያየት ላይ የተመረኮዙ ጥናቶችን (polls) የማካሔድ፣ ከሬዲዮው አድማጮች እና ከድረ ገፁ ተከታታዮች ጋር ቀና የሆነ መስተጋብር የመፍጠር አገልግሎት ይኖራቸዋል።

የአሐዱ ሬዲዮ ተልዕኮ እንዲሳካ የሚያግዙን፣ ሌሎች ዕድሎቻችን አብረውን እንዲሠሩ በጥንቃቄ የመረጥናቸው ተባባሪ አዘጋጆቻችን ናቸው። እነዚህ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ልምድ ያካበቱ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች ትምህርታዊ እና አዝናኝ ፕሮግራሞቻቸውን አሰናድተው፣ በአሐዱ በኩል ከአድማጮች ሊገናኙ ተዘጋጅተዋል።

አሐዱ ሬዲዮ ቀድመውት እየተደመጡ፣ እየታዩ እና እየተነበቡ ያሉትን መገናኛ ብዙኃን እንደሙያ አጋሮቹ ስለሚቆጥራቸው፣ እና የእነሱ ስኬቶች ለበለጠ ስኬት እንደሚያተጋው ስለሚያምን፣ ምን ጊዜም ቢሆን ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ለመሥራት በሩን ክፍት አድርጎ ይጠብቃል፤ የአብረን እንሥራ ጥሪውንም ያስተላልፋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15469 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 728 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us