ደራሲ ማን ነው?

Wednesday, 28 June 2017 11:36

 

በጥበቡ በለጠ

 

ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አመታዊው ንባብ ለሕይወቱ የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ ይካሄዳል። በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ በርካታ መፅሐፍት አከፋፋዮች፣ ደራሲያን፣ አንባቢያን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎችም ሠዎች ይታደሙበታል። ንባብ ለሕይወት የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ብዙ የሚጥር ፕሮግራም ነው። ከብዙሃን መገናኛ ጋር እና ከደራሲያን ጋር አያሌ ተግባራትን ያከናውናል። ከዚህ ቀደም በደራሲነት እና በድርሰት ላይ ውይይት መደረጉ ትዝ ይለኛል። እሱን መሠረት አድርጌ ዛሬ ደራሲ ማን ነው በሚል ርዕስ እስኪ እንጨዋወት።

 

ይህን ርዕስ መርጦ አንድ ፅሁፍ ለመፃፍ የማይሞከር፣ የማይገፋ ሀሳብ ለማስተናገድ እንደመሞከር ነው። በጣም ሰፊ ነው። ከየቱ ተጀምሮ የትኛው ላይ ማቆም እንዳለብን ሁሉ አይታወቅም። ነገር ግን እስኪ አንድ ዳሰሳ እናድርግና ወደ ቀጭኑ ወይም ጠባቡ መስመር እየገባን እሱንም እያደማነው፣ እየመረመርነው እንሂድ በሚል የሩቅ አላማ ተስፈኛ ሆኜ ነው ዛሬ የተነሳሁት።
አንድ ጊዜ የቅርብ ወዳጄ የሆነ ሰው “ኢትዮጵያ ደራሲዎቼ ብላ የምትቆጥረው ከማን ጀምሮ ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። እንደሚመልስ ሰው Well! ብዬ ቀረሁ። ሳስበው አጣብቂኝ ጥያቄ ነው። ወደኋላ ሄዶ ሉሲን ድንቅነሽን ይዛ መጥታ የሰው ልጅ መገኛ፣ የዓለም ቁንጮ ነኝ ብላ የሦስት ሚሊዮን አመት ታሪክ መዛ የተቀመጠች ሀገር የደራሲዎቿስ መነሻ ከየትኛው ክፍለ ዘመን ላይ ይነሳል?። ከዚያው ከነጋድራስ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ጦቢያ፤ እንጀምር ወይስ ሌሎች ጐምቱ ደራሲዎች ከርሱ በፊት ነበሩን? አዎ ነበሩን ማለት ይቻላል። ነገር ግን ደራሲ ማለት በራሱ ምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች ደራሲን ከፈጠራ ሙያ ጋር ያያይዛሉ። ደራሲ ፈጣሪ ነው ይላሉ። ደራሲ ገፀ-ባህሪያት ፈጥሮ፣ ታሪክ አበጅቶላቸው፣ መኖሪያ ስፍራ ሰጥቷቸው፣ እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲተነፍሱ፣ እንዲያወሩ፣ የዚህችን ውጣ ውረድ የበዛባትን ዓለም መከራ መቋቋም ካልቻሉ እንዲሞቱ የሚያደርግ ሰው ነው የሚሉ አሉ። በዚህ ብያኔ የሚፀኑት ሰዎች የታሪክ ሰነዶችን የሚመዙት የልቦለድ ስራዎችን ከፃፉ ደራሲዎች አንፃር ነው። ይሄ ደግሞ 1900 ዓ.ም ላይ ያርፍና ከዚያ ላይ ነው የሚነሳው። ይህን ሀሳብ የሚደግፉት ሰዎች ሌላም ነጥብ ያነሳሉ። ደራሲ የሚባለው ሰው መፅሀፍ ፅፎ ያሳተመ፣ ያሰራጨ፣ ወይም አንባቢያን ዘንድ ያደረሰ መሆን አለበት ሲሉ ሰምቻለሁ።


ሌሎች ይነሱና ደግሞ ያላሳተመ ሰው ‘ደራሲ’ እንዴት ነው ሊባል የማይችለው ብለው ቡራ ከረዩ ይላሉ። ለምሳሌ እንደ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ያሉ ሰዎች የፃፏቸው ድርሰቶቻቸው በተለያዩ እክል ምክንያት ለ30 አመታት ቁጭ ካሉ በኋላ ነው የህትመት ብርሃን ያዩት። እና እነስብሃት አጋጣሚዎች ተሳክቶላቸው ባያሳትሙ ኖሮ ደራሲ ላይባሉ ነው? ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ አያሌ ናቸው። ለነገሩ ለእነዚህ አይነት ደራሲዎች እንግሊዝኛው “Un Published Writer” ይሏቸዋል። ‘ያላሳተመ ደራሲ’ እንደማለት ነው።


ከዚህ ሌላ ደግሞ ከፈጠራ ፅሁፍ ባሻገር ያለውን ስራስ የሚሰራው ሰው ምን ሊባል ነው? ብለው የመከራከሪያ ነጥብ መዘው የተነሱ ሰዎች አሉ። መፅሀፍ አሳትመው ለልጅ ላዋቂው ከስነ-ምግባር እስከ ታላላቅ ፍልስፍና ያስተማሩ ያሳወቁትስ ምን ልትሏቸው ነው? ሃይማኖትን ተመርኩዘው፣ ከሃይማኖት ጐን ቆመው ሃይማኖታዊ ወግና ስርአትን ለማስተማር ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን እየፈጠሩ፣ እየተረኩ ያሳወቁ ያስተማሩ አበው ምን ሊባሉ ነው?


ክርክሩ ማብቂያ የለውም። አጨቃጫቂው ደራሲ የሚለው ቃል ነው። ደራሲንና ፀሐፊን ለይታችሁ ተናገሩ የሚሉም አሉ። ደራሲ የሚባለውን ከፈጠራ ፅሁፍ ጋር ብቻ ያቆራኙታል። ፀሐፊ የሚባለው ደግሞ ይሄው እኔ እንደምፅፈው አይነት ፅሁፎች ላይ የሚያተኩረውን መግለጫ ነው። ቃል ብዙ ነገር ይጠራል።
አሁን አሁን ደግሞ መፅሀፍ ማለት ምን ማለት ነው እየተባለ ነው። አንድ መፅሀፍ፤ መፅሀፍ ለመባል ማሟላት የሚገባው መስፈርት አለ። ከነዚህ መስፈርቶች አንዱ የገፅ ብዛቱ እና የመፅሀፉ መጠን ነው የሚሉ የስነ-ፅሁፍ ምሁራን አሉ። በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጽ ብዛታቸው በጣም አናሳ የሆኑና እንዲሁም ቅርፃዊ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ‘መፅሀፎች’ እየታተሙ ነው። እነዚህ መፅሀፍ ሊባሉ አይችሉም እየተባለ ነው። ነገሩ እንዲህ አይነት መፅሀፍትን ማሳተም በሀገራችን ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በተለይ 1950ዎቹ ውስጥ በስፋት ተስተውሏል። ይህ የ1950ዎቹ ሁኔታ ናይጄሪያ ውስጥ ከነበረው የድርሰት አብዮት ጋር አብሮ የሚነሳ ነው።


ናይጄሪያ ውስጥ በ1950ዎቹ ‘ኦነትሽያ ማርኬት’ የሚባል መጠሪያ የተሰጠው ‘የስነ-ፅሁፍ ገበያ’ ነበር። ይህ ሁኔታ እንዲህ ነው፡-
አስርም ይሁን ሃያ ገጽ ያላቸው መፅሀፎች በብዛት ይታተሙ ነበር። እነዚህ ለንባብም ሆነ ለዋጋ ርካሽ ስለነበሩ በጣም ይነበቡ ነበር። የናይጄሪያም ስነ-ፅሁፍ ሲጠራ ይሄ ዘመን አብሮ ይወሳል። የደራ ‘የስነ-ፅሁፍ ገበያ’ የነበራት ወቅት ነውና። ታዲያ በዚያን ዘመን በእኛም ሀገር እንዲህ አይነት ፅሁፎች እንደበሩ በሙሉ ድፍረት መናገር በሚያስችል መረጃ ማውጣት ይቻላል። ዛሬ ዛሬም ይህ ሁኔታ ብቅ እያለ ነው።


ይሄ እንግዲህ ደራሲ የሚባለውን ስብዕና ብያኔ ለመስጠት ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉና እንዲሁም ደግሞ አንድ መፅሀፍ በራሱ፣ መፅሀፍ ለመባል የደረጃ መመዘኛ እንዳለው የሚያሳስቡ ድምጾች ብቅ ብቅ ማለት ስለጀመሩ እንደ መወያያም ያገለግለናል። በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማለት ነው።


ድሮ ድሮ ልበልና ከ1920ዎቹ በፊት የደራሰዎቻችን ሙግት ነበር። የዕውቀት ክርክር። ለምሳሌ ያህል ደራሲ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ስለ አፄ ምኒልክ በፃፉት መፅሀፋቸው ውስጥ የምኒልክን ጀግንነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ብልህነት ወዘተ. በጥልቀት ዳሰዋል። አፈወርቅ በዚህ ብቻም አላበቁም የምኒልክን ታሪክ ሲፅፉ አፄ ቴዎድሮስን በቃላት ጐነጥ አድርገው አልፈዋል። ታዲያ ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ደግሞ ሌላ ደራሲ መጣባቸው። ገብረህይወት ባይከዳኝ።


ገብረህይወት ባይከዳኝ በዚያን ዘመን ከነበረው ማህበረሰብ አንፃር ህዝብን እንደ ህዝብ የሚወቅስበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ገብረህይወት ‘የኛ ህዝብ የሚሠራለትን፣ ጐበዝ የሆነን ሰው አይወድም። የሚወደው ሰነፍ፣ ወይም መጥፎ የሆነውን ነው’ የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ይሰነዝር ጀመር።


እናም ስለ አጤ ምኒልክ ታሪክ የተፃፈውን መፅሐፍ ተችቷል። አጤ ምኒልክን ለማሞገስ ቴዎድሮስ መሰደብ የለባቸውም ብሎ የተነሳ ሰው ነው። እንደ ገብረህይወት አባባል አጤ ምኒልክ የተወደዱት ጐበዝ በመሆናቸው አይደለም። ጐበዝ የሆነማ ሰው አይወደድም እንዲያውም በተቃራኒው ያለው ነው የሚወደደው ይል ነበር።


ይህንን ሀሳቡንም ሲያጠናክር በዚያን ዘመን ወደ ሐረር አካባቢ የነበረን ክስተት ያስታውሳል ገብረህይወት። እንደ ገብረህይወት አፃፃፍ አንድ ብልህ ሰው ሐረር ውስጥ ለሰዎች መሬት ትሽከረከራለች ብሎ ሊያስረዳ ይሞክራል። ህዝቡ ደግሞ “አቤት ውሸት፣ አይ ዘመን እንዳው የቀጣፊዎች ሆኖ አረፈው? ይሄው በአይናችን የምናያትን ፀሐይ በምስራራቅ ወጥታ በመዕራብ የምትጠልቀውን ትቶ ንቅንቅ የማይለውን መሬትን ይሽከረከራል ይላል። “ቀጣፊ” ተብሎ ሰውየው ተተቸ። አይንህ ለአፈር ተባለ። የሚገርመው ነገር ሰውየው ጭራሽ ታሰረ። መሬት ትሽከረከራለች በማለቱ።


ገብረህይወት ባይከዳኝ የኛ ህዝብ እንዲህ ነው አዋቂውን አያስጠጋም። እንዲያውም ያስረዋል። ስለዚህ እዚህ ሀገር ሰው የሚጠላው ሰው ጥሩ ነው ማለት ነው እያለ ተጠየቅ ሎጂክ ያዘለ ክርክር ጀምሮ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ህዝብ የጠላቸው ጐበዝ ስለነበሩ ነው የሚል እሳቤም ነበረው።
የሁለቱ ደራሲዎቻችን ክርክር ዛሬ ላይ ቁጭ ብለን ስንመለከተው በራሱ ታላቅ የፈላስፎች ጉባኤ ይመስላል። ሁለቱም ሰዎች በዘመናቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ዘመናዊውን ትምህርት ቀስመው፣ እውቀት አዳብረው ከመጡ በኋላ ነው የሀሳብ ሙግት ውስጥ የገቡት።
አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከያኒ ልንለው የምንችለው ሰው ነው። በሁሉም መስክ የተዋጣለት ነበር። ልቦለድ ደራሲ ነው። ፀሐፌ ተውኔት ነው፣ ምርጥ ሰአሊ ነው፣ የታሪክ ፀሐፊ ነው፣ ጋዜጠኛም ነበር በህይወቱ ፍፃሜ አካባቢ።


አፈወርቅ ገ/እየሱስ ሰብዕናው በስርአት መፈተሽ አለበት። ይህንን ስል ለምሳሌ ምኒልክና የኢጣሊያ መንግሥት ውጫሌ 17 ውል ተፈራርመው ሲጨርሱ አፈወርቅ ሮም ከተማ ውስጥ ነበር። ያ ውል ሲደርሰውም የትርጉም መዛባት እንዳለበት ተገነዘበ። መገንዘብ ብቻም ሳይሆን የተፈፀመውን ስህተት ደብዳቤ ፅፎ ለምኒልክ ያሳወቀ ሰው ነው። ከዚያም የአድዋ ጦርነት እንዲነሳ ሆነ። ታዲያ አፈወርቅ ገ/እየሱስ የአድዋ ጦርነት እንዲነሳ የመቀስቀሻ ደውል ያሰማ ሰው ነው ማለት ይቻላል።


ከአድዋ በኋላ ያለው አፈወርቅ በጥበብ የተራቀቀ ነው። ለምሳሌ ለሀገራችን የዘመናዊ ስዕል አሳሳል ፈር ቀዳጅ ነው። አያሌ ስዕሎችን ሸራ ወጥሮ አበርክቷል። በፀሐፌ ተውኔትነቱም ልዩ ልዩ ቴአትሮችን አበርክቷል። ነገር ግን ዛሬ ዛሬ እነዚህ ፅሁፎች የሉም። ንብረቶቹ በተለይም ለኢጣሊያ በባንዳነት አድረሃል በሚል ሰበብ ከወረራው በኋላ ተዘርፈዋል። ወይም ሆን ተብለው ተቃጥለውበታል። አሁን ድረስ እጃችን ላይ ቢኖሩ አያሌ ጥናቶችና ምርምሮችም መነሻቸው የአፈወርቅ ተውኔቶች ይሆኑ ነበር።


አፈወርቅ ገ/እየሱስ በስዕል ስራው እንግልትና መከራ የደረሰበት ሰው ነው። ለቤተ-መንግሥት ቅርብ በመሆኑ የአጤ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱን መልክ በስዕል ያስቀምጠዋል። በወቅቱ ፎቶ ግራፍ እምብዛም ስለሌለ ስዕል ዋነኛው የምስል ማኖሪያ ጥበብ ነበር። ከእቴጌ ጣይቱ ጋርም የቅርብ ዝምድና ነበረው። ታድያ እቴጌን ሲስል አንድ ያልተጠበቀ ነገር ብቅ አደረገ። እቴጌ ጣይቱ ጥርሳቸው በተፈጥሮ ወደፊት ወጣ ያለ ነው። አፈወርቅ ደግሞ ይህንን ጥርስ በስዕል ያሳያል ብሎ ያሰበ የለም። እናም እንዳለ ሳለው። እቴጌ ተቆጡ፤ ቁጣም ብቻ ሣይሆን ቅጣትም ደርሶበታል።
አፈወርቅ በዚህ አዝኖ የምኒልክና የጣይቱ ባላንጣ አልሆነም። ለስርዓቱ ቀረብ ብሎ ብዙ ነገር አበርክቷል። ከምኒልክ ስርአት በኋላ በመጣው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ደግሞ ፍፁም የተለየ ስብዕና ተላብሶ ብቅ አለ።


ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ከወራሪዋ ጋር አብሮ ተሰለፈ። በዘመኑ አጠራርም ባንዳ ተባለ። ባንዳ የተባለበት ሁኔታ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን መላ ግዛት በወረራ ስትይዝ ህዝቡ ፀጥ ረጭ ብሎ ካለ ሁከት እንዲኖር አፈወርቅ ሰባኪ እንዲሆን ተደረገ። እሱም እሺ አሜን ብሎ ተቀበለው። በወቅቱ በኢጣሊያኖች አማካይኝነት ይታተም የነበረውን “የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ” የተሰኘውን ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት መስራት ጀመረ።


ጋዜጣው በስፋት የሚያተኩርባቸው ርዕሰ ጉዳዮች የኢጣሊያኖችን ቅዱስነት፣ የጥበባቸውን ርቀት፣ የስልጣኔያቸውን ልዕለ ኃያልነት፣ ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦቿ ያላቸውን ፅኑ ፍቅር ወዘተ በጐ ነገሮችን ያወሳል። ከዚህ ሌላ ደግሞ ወራሪዋን ኢጣሊያን ለመመከት በአርበኝነት ወደ ጫካ የገቡትን ተዋጊዎች አለማወቃቸውን፣ በአስተሳሰብ ወደ ኋላ የቀሩ እንደሆኑ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ይፅፍ ነበር። አርበኞቹን ኑ ወደ ቤታችሁ ግቡ፣ ጫካ ለጫካ ምን አንከራተታችሁ እያለ ይሰብካቸው ነበር።


ከአድዋ ጦርነት በኋላ እስከ ሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ድረስ 40 ዓመታት ተቆጥረው ነበር። እናም አፈወርቅ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን አስተዳድራ ቢሆን ዛሬ ዛሬ ሀገሪቱ የታላቆች ታላቅ ትሆን ነበር በማለት ኃይለኛ ሰበካ ያካሂድ ነበር። እንደውም “አርባ ዓመት ያለጥቅም አለፈ” በሚለው መጣጥፉ ይህንኑ ጉዳይ አብራርቶ ፅፏል።


አንዳንድ ሰዎች ስለ አፈወርቅ ስብዕና ሲናገሩ ሰውየው የሀገሩን እድገት ስልጣኔ በጣም የሚፈልግ ነበር። አውሮፓ ሄዶ ስለተማረ የዓለምን የእድገት ደረጃ አይቷል። ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ደግሞ ሲመለከት የኢንዱስትሪውም አብዮት ሆነ ልዩ ልዩ የእድገትና የብልፅግና ዘውጐች የሏትም። እናም ጣሊያኖች ቢገዙን ሳይሆን ቢያስተዳድሩን ካለንበት ደረጃ አፈትልከን እንወጣለን የሚል አመለካከት ነበረው ይላሉ። ይህ አባባል በብዙዎቹ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚያመጣ መናገር ይቻላል።


ሌላው የሚገርመው ነገር በዚሁ አፈወርቅ በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ አምደኞች የነበሩ ታዋቂ የኢትዮጵያ ልጆች መኖራቸው ነው። ለምሳሌ ታዋቂው ደራሲ ከበደ ሚካኤልና ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የፃፏቸው መጣጥፎች አሉ። ተሰማ እሸቴ የኢጣሊያኖተን ስልጣኔና እውቀት ዘርዝረዋል።


በአጠቃላይ ግን የሀገሩን እድገትና ስልጣኔ የማይመኝ የማይናፍቅ የለም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ስልጣኔው በየትኛው መንገድ ይሁን የሚለው የአቅጣጫ ምርጫ ነው ልዩነት የሚያመጣው። በአሁኑ ጊዜ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ እና ‘ሊብራል ዴሞክራሲ’ የሚሉ አስተሳሰቦች እያንዳንዳቸው ለእድገት ይሆኑኛል የሚሏቸውን ነጥቦች ይጠቅሳሉ። የድሮውም አስተሳሰብ አፋጣኝ እድገት ለማግኘት ‘በሰለጠነው’ ኃይል ተገዝተን እንደግ የሚል የአፈወርቅ ሀሳብና ኧረገኝ እንዴት ተደርጐ በቅኝ ተገዝቼ እኖራለሁ? በነፃነቴ ራሴን እየመራሁ ቆሎም ቆርጥሜ እቀጥላለሁ የሚሉ ፅንፎች ነበሩ። ጉዳዩ አጨቃጫቂ ነው።


እንግዲህ አፈወርቅ ገ/እየሱስ የመጀመሪያው የአፍሪካ ልብወለድ መፅሀፍ ደራሲ ነው ይባላል። ጦቢያ። የአጤ ምኒልክንም ታሪክ ፅፏል። ከጥበብ ጋር ኖሯል። አሳይቷል፤ አስተምሯል።
ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ምድር ተሸንፋ ተባራ ስትወጣ አፈወርቅ ግን ያው ሀገሩ ኢትዮጵያ ቀረ። ሽምግልናም አይሎበት ደክሟል። ግን ታሰረ። በግዞት ኖረ። ተሰቃየ። የዓይን ብርሀኑንም አጥቷል። የህይወት ውጣ ውረድን በብዕሩ እንዳሳየ ሁሉ በዕውናዊ ህይወቱም እላይ አታች ብሎ ይህችን ዓለም 1939 ላይ ተሰናበተ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15505 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1049 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us