የአፍሪካ የእስልምና ሐይማኖት ማዕከልና የስልጣኔዋ ማማ ቲምቡክቱ - ማሊ

Wednesday, 21 June 2017 13:43

 

በጥበቡ በለጠ

ቲምቡክቱ የምትባለዋ ከተማ ማሊ ውስጥ የምትገኝ ናት። ማሊ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች መካከል አንዷ ነች። ቲምቡክቱ በውስጧ የያዘቻቸው እጅግ ውድ ቅርሶች የሚባሉ ፅሁፎችን ነው። እነዚህ ፅሁፎች አብዛኛዎቹ ከእስልምና ሀይማኖት ጋር የተገናኙ እና በእምነቱ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዘው የተዘጋጁ ናቸው። በዚህ የተነሳ ቲምቡክቱ እና በውስጧ የያዘቻቸው ቅርሶች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /UNESCO/ አማካይነት የዓለም ቅርስ ሆነው ተመዝግበዋል። እነዚህ ብርቅዬ ቅርሶች በጦርነት ምክንያት እየጠፉና እየተበላሹ ይገኛሉ። ዛሬ ቲምቡክቱን በአጭሩ እንቃኛታለን።

ቲምቡክቱ በአፍሪካ ውስጥ የጥንት ስልጣኔ ታሪክ ሲነሳ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎችም ሐገሮች ጋር አብራ ብቅ ትላለች። የቲምቡክቱ ሥልጣኔ የፅሁፍ ነው። በተለይም ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ላይ ተመርኩዘው በሚፃፉ አስተሳሰቦችና ፍልስፍናዎች ላይ እጅግ በርካታ ቅርሶች አሏት። ይህች ከተማ ከ13ኛው እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የእስልምና ሃይማኖት የትምህርት ማዕከል ነበረች። በዚህም የተነሳ ከተለያዩ የጎረቤት ሀገሮች ለምሳሌ ከሞሪታኒያ እና ከሌሎችም ተማሪዎች ወደ ቲምቡክቱ እየመጡ ይማሩ ነበር። የቁርአን ትምህርትና የእስልምና ሃይማኖት ስርዓቶች ሁሉ እውቀት የሚገኝበት ጥንታዊ ከተማ ነች።

ጥንት ቲምቡክቱ ውስጥ የተፃፉ መፃህፍት በአንድ ወቅት ተሰባስበው በላይብረሪ ውስጥ ተቀምጠዋል። እነዚህ መፃህፍት በቁጥር 700 ሺ እንደሆኑም ተገልጿል። ይህ ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ የሚባል ነው። እነዚህ 700 ሺ ፅሁፎች /manuscripts/ በውስጣቸው የያዟቸው በርካታ ቁም ነገሮች ገና ተመርምረው አላለቁም። ዓለም በቅርስነት የመዘገባቸውን እነዚህን ብርቅዬ ፅሁፎች በጥር ወር ላይ የተነሱት የማሊ የእስልምና ሃይማኖት አክራሪ ቡድኖች አብዛኛዎቹ ላይ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ታውቋል። የተቃጠሉ፣ የተበላሹ፣ የተዘረፉም እንዳሉ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

ቲምቡክቱ ትንሽዬ ከተማ ብትሆንም የእውቀት ከተማ ነች። በውስጧ 60 ቤተ-መጻህፍት አሏት። በነዚህ ቤ-መጻህፍት ውስጥ የተጨናነቁት ደግሞ እነዚህ 700 ሺ ማኒስክሪብቶች ነበሩ። የቲምቡክቱ ጎብኚዎች ዋነኛ ዓላማቸውም የጥበብና የፅሁፍ ሀገር መሆኗን ለማየት ለማንበብ የሚጓዙ ናቸው። በአፍሪካ የፅሑፍ ስልጣኔ ውስጥ እንደ ኮከብ የምታበራው ይህች ከተማ ዛሬ የጦር ሰራዊት የሚርመሰምስባት ሆናለች።

የቲምቡክቱ ፅሁፎች ከ13ኛው እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ያሉትን የታሪክ፣ የአስትሮኖሚ፣ የማቲማቲክስ /የሂሳብ ቀመር/፣ የፊሎሶፊ፣ የጂኦግራፊ እና የሌሎችንም ርዕሰ ጉዳዮች የያዙ ናቸው።

ቲምቡክቱ ማሊ ውስጥ ከሚገኙ ስምንት የአስተዳደር ክልሎች መካከል አንዷ ናት። ከኒጀር ወንዝ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች ጥንታዊ ከተማ በውስጧ 54 ሺ 453 ህዝብ ይኖራል። በከተማዋ ያሉት ፅሁፎች ግን 700 ሺ ናቸው። የፅሁፍ ጥበቧ ከህዝቧ ቁጥር በእጅጉ የሚልቅ አስገራሚ ከተማ ነች። ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የእስልምና ማዕከል ሀና ብቅ ያለችው ይህች ከተማ ሌሎችም የንግድ እንቅስቃሴዎች ይካሔዱባት ነበር። ለምሳሌ የባሪያ ፍንገላ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅ እንዲሁም የጨው ንግድ በሰፊው ይሰራበት የነበረች የምዕራብ አፍሪካ ባለታሪክ ነች።

ቲምቡክቱን የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች እ.ኤ.አ በ1893 ዓ.ም በቅኝ ግዛት ማስተዳደር እስከጀመሩበት ወቅት ድረስ በርካታ ገዢዎችን እና ስርወ መንግስቶችን አስተናግዳለች። ከነዚህ ውስጥ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቱአርግ /Tuareg/ ነገዶች ይዘዋት ቆይታለች። ከዚያም 1468 ዓ.ም የሶንግሀኢ መንግስተ- ግዛት /Songhai Empire/ ተመስርቶባት ሲያስተዳድራት ነበር። በ1591 ደግሞ የሶንግሀኢ መንግስተ-ግዛት ወድቆ ሳዲ /saadi/ የሚባል ስርወ መንግስት ተመሰረተ። ሌሎችም አስተዳደሮች ሲፈራረቁባት ቆይታለች። ነገር ግን የእስልምና ሃይማኖት የእውቀት ማዕከልነቷን እንደጠበቀችና እንዳስፋፋች ለዘመናት ኖራለች።

በቅርቡ ማሊ ውስጥ የተነሱት የእስልምና አክራሪ ተዋጊዎች ቲምቡክቱን በእጅጉ አጠቋት። በውስጧ ያሉትን እነዚህን ብርቅዬ ሰነዶች ጉዳት አደረሱባቸው። ምክንያታቸው ደግሞ እነርሱ ከሚያራምዱት የአክራሪነት መንፈስ ጋር አብረው የሚጓዙ ሰነዶች አይደሉም። ፅሁፎቹ የጥናትና የእውቀት ውቴቶች ናቸው። አክራሪዎቹ ደግሞ የጦርነት ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ ሁለቱ የማይታረቁ ባላንጣዎች ሆነው የቲምቡክቱ ቅርሶች ለጉዳት ተጋልጠዋል።

አክራሪዎቹ ቅርሶች አሉበት ተብሎ የሚታወቀውን የአህመድ ባባን ኢንስቲቲዩትም አቃጥለዋል። ይህ የአህመድ ባባ ኢንስቲቲዩት የተሰራው በደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ድጋፍ ነበር። በውስጡም 30ሺ ጥናታዊ ፅሁፎች /manuscripts/ ይገኙ ነበር። የBBC ዜና ዘጋቢ ከስፍራው እንደጠቆመችው ከሆነ ደግሞ ከ28 ሺ በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች አክራሪዎቹ ከማቃጠላቸው በፊት ካሉበት ቦታ ወጥተው ሌላ ሚስጢራዊ ስፍራ ተቀምጠዋል እያለች ነው። ግን የተወሰኑት ደግሞ መውደማቸው እየተነገረ ነው።

የአህመድ ባባ ኢንስትቲዩት እንዲቋቋም የገንዘብ እና የማቴሪያል ድጋፍ ያደረገችው ደቡብ አፍሪካ ናት። በተለይም የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ታምቦ ኢምቤኪ ያደረጉት ውለታ በሰፊው ተዘግቦም ይገኛል።

በቲምቡክቱ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጥንታዊ ፅሁፎች ዋጋቸው በገንዘብ አይለካም። በእንግሊዝኛው /priceless Heritages/ በመባል የሚጠሩ  ናቸው። ምክንያቱም የተዘጋጁበት ዘዴ እና በውስጣቸው የያዙት ቁም ነገር እጅግ ውድ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ ጥራዛቸው በወርቅ የተለበጡ ጽሑፎች አሉ። የዓለምን የሥነ-ፈለክ /አስትሮኖሚ/ ሁኔታ በልዩ ልዩ ቻርቶችና ስዕሎች የሚያሳዩ ፅሁፎች አሉ። እድሜያቸውም ወደ 800 ዓመታት ይጠጋል። ከዚህ ሌላ የሒሳብ ቁመሮችን (ፎርሙላዎችን) የያዙ ጥንታዊ ፅሁፎች አያሌ ናቸው። የህክምና ሳይንስን በጥንታዊ ሰዎች እሳቤ እንዴት እንደነበር የሚያስረዱ ፅሁፎች፣ ሃይማኖታዊ መረጃዎች፣ የህግና የደንብ ፅሀፎች፣ መንግስታዊ አስተዳደሮች፣ የቋንቋ ስዋስው /Grammar/፣ እና ጂኦግራፊን የያዙ ናቸው።

የቲምቡክቱ ፅሁፎች በአረብኛ ፊደላት የተጻፉ ናቸው። የተፃፉበት ቋንቋ ግን በአረብና እና በሌሎችም የአፍሪካ ልሳናት ነው። እነዚህ ፅሁፎች በዚያው በማሊ ውስጥ የተዘጋጁ እና ከሌሎችም ሀገሮች በልዩ ልዩ ምክንያት እየተሰበሰቡ የተከማቹ ናቸው።

ዛሬ በስሙ ቤተ-መፃህፍት የተከፈተለት አህመድ ባባ በቲምቡክቱ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ዝነኛ ሰው ሆኖ ይጠራል። ምክንያቱም ይህ ሰው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የታወቀ የቲምቡክቱ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ ነበር። ይህ ሰው ለብቻው ከ1600 ጥንታዊ ፅሁፎችን ያዘጋጀና ያሰባሰበ የፅሁፍ ሊቅ ነበር። ቤተ-መፃህፍትም ያቋቋመ ሰው ነው። ዛሬ በስሙ የደቡብ አፍሪካ መንግስት /Ahmed Baba Institute/ የሚል ተቋም ቲምቡክቱ ውስጥ ከፍቶለታል። አህመድ ባባ የአፍሪካ አህጉር የፅሁፍ ጥበብ መፍለቂያ እንደነበረች የሚመሰክር ባለውለታ ሆኖ ስሙ ይጠራል።

ማሊ የጥበብና የፅሑፍ የታሪክ ሀገር ነች። የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት አልፋ ኦማር ኮናሬ ራሳቸው በቲምቡክቱ ታሪክ እየተመሰጡ ያደጉ ናቸው። እስከ ፕሮፌሰርነት እስከሚደርሱ ያጠኑ የነበሩት ታሪክን፣ ጂኦግራፊንና እንዲሁም የአርኪዮሎጂ ትምህርቶችን ነበር። የቲምቡክቱ የጥበብ ምድርነት ፕሮፌሰር አልፋ ኦማር ኮናሬን አስተምሮ እስከ ፕሬዚዳንትነት አድርሷቸዋል።

ቲምቡክቱ የአፍሪካን የፅሁፍ ስልጣኔ ጮክ ብላ የምትናገር የጥበብ ምድር እንደሆነች በተለያዩ ጊዜያት ሲገለፅ ኖሯል። የቲምቡክቱ አህመድ ባባ ኢንስቲቲዩት ፕሬዚዳንት የሆኑት መሐመድ ዞብር እንደሚናገሩት፣ አውሮፓውያን ተስፋፊዎች ወደ አፍሪካ የመጣነው አህጉሪቱን ለማሰልጠን ነው ይላሉ። ነገር ግን  ቲምቡክቱ የአፍሪካን የቀድሞ የስልጣኔ ብርሃንን የምታሳይ እንደሆነች ተናግረዋል።

Colonizers had always argued that they were here to civilize Africa.

But there were many points of light clearly Africa was not living in obscurity

 

 

 

ሙስሊሟ ኢትዮጵያ

 

ኢትዮጵያ ውስጥ አያሌ ሐይማኖቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን ክርስትና እና እስልምና ይጠቀሳሉ። ሁለቱም ሃይማኖቶች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ተከታዮች አሏቸው። ሁለቱም ሃይማኖቶች መሠረታቸውን ከውጭ ሀገር ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን የራሳቸውን ማንነት እና መገለጫ ይዘው ነው።

የራሳቸው መገለጫን ይዘው ነው የገቡት ሲባል ኢትዮጵያዊ ሃይማኖቶች ናቸው ለማለት ፈልጌ ነው። ሁለቱም ሃይማኖቶች በጦርነት ወይም በግዴታ (በተፅዕኖ) ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የተስፋፉ አይደሉም። እንደውም ኢትዮጵያዊያኖች ፈቅደውና ደስ ብሏቸው ወደ ሀገራቸው ይዘዋቸው ገብተዋል በማለት የተለያዩ ደራሲያን ፅፈዋል።

ለምሳሌ የክርስትናውን ሃይማኖት ታሪክ ስናነብ መነሻችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሐዋርያት ስራ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ኢትዮጵያዊ አለ። ይህም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እየሩሳሌም ሔዶ ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ የክርስትናን ሃይማኖት አስፋፍቷል። ጃንደረባው በወቅቱ የኢትዮጵያ የገንዘቧ አዛዥ ነው ይባላል። ይህ ማለት በአሁን አጠራር የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ሚኒስትር እንደማለት ነው። ስለዚህ ካለማንም ተፅዕኖ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሃይማኖቱን ወደ ሀገሩ ይዞ ገብቶ አስፋፍቷል ማለት ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊ ንጉስንም ማንሳት ይቻላል። አፄ ባዜን ይባላል። ይህ ንጉስ ከአክሱም ዘመን ነገስታት አንዱ ነበር። እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ባዜን ኢትዮጵያ ውስጥ ገናና መሪ ነበር። ታዲያ የእየሱስን መወለድ ሲሰማ በጣም ደስ ብሎት ሠራዊቱን አሰልፎ ወደ እየሩሳሌም እንደሄደ ታሪኩ ያወሳል። እዚያም እንደደረሰ የዓለም ጌታ ተወልዷል ደስ ብሎኛል ብሎ የወርቅ ስጦታዎችን አበርክቶ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለስምንት ዓመታት ነግሷል። በዚህም ጊዜ ክርስትናን ለሀገሩ ህዝብ አስተዋውቋል፣ አስተምሯል የሚሉ ፀሐፊዎች አሉ።

በአጠቃላይ ሲታይ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እንደ ሌሎቹ ሀገሮች በጦርነት እና በቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ አይደለም። ኢትዮጵያዊያኖች ራሳቸው ወደውና ፈቅደው ተቀብለው ከዚያም በራሳቸው ባህልና አስተሳሰብ አስፋፍተውታል።

በእስልምናውም ሃይማኖት ብንመጣ ከዚህ የተለየ ነገር አናገኝም። እንደውም የእስልምናው ደግሞ ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉት። ሃይማኖቱ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያዊያኖች ሆኖ እናገኘዋለን። ታሪኩ እንዲህ ነው።

በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ታላቁ ነብይ መሐመድ ይጠቀሳሉ። እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ገና በህፃንነታቸው እናታቸው እንዳረፉባቸው ይገለፃል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሞግዚቶች ይቀጠሩላቸዋል። ከተቀጠሩት ሞግዚቶች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ እሙአሚን አል ሐበሻ ይጠቀሳሉ። እሙአሚን አልሐበሻ በነብዩ መሐመድ ህይወት ውስጥ ትልቅ ታሪክ አላቸው። እሙአሚን ነብዩ መሐመድን እንደ እናት ሆነው ጡት እያጠቡ እንዳሳደጓቸው ታሪክ ያወሳል። በዚህም ምክንያት ነብዩ መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ ማንነት እና ታሪክ እንደራሳቸው ሀገር አውቀው ነው ያደጉት እየተባለ በልዩ ልዩ መፃህፍት ውስጥ ተጠቅሷል።

አንዳንድ መፃሕፍት እንደሚያወሱት ከሆነ ነብዩ መሐመድ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በተነሱ ጊዜ አብረዋቸው የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑም ይገልፃሉ። እንደ እናት ሆነው ያሳደጓቸውን እሙአሚን አል ሀበሻን ተከትለው የሄዱ ኢትዮጵያዊያን ስለነበሩ በነብዩ መሐመድ እንቅስቃሴ ወቅት እንደ ጠባቂ እና አማኝ ሆነው እስልምና ሃይማኖት ኢትዮጵያዊያን አስፋፍተውታል ተብሎ ተፅፏል።

በዚህ ምክንያት ነው ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸው ለአደጋ ሲጋለጡባቸው “ወደ ኢትዮጵያ ሒዱ። እዚያ በሰላም ትኖራላችሁ። መልካም ንጉስ አለ” ብለው ቤተሰቦቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የላኩት። ነብዩ መሐመድ እንዲህ ያሉበት ምክንያት ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊቷ እሙአሚን አልሐበሻ አማካይነት በማደጋቸው ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ያውቋታል ማለት ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ከተባሉት የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች መካከል ሴት ልጃቸው ሩቅያ፣ ባለቤቷ ዑስማን ኢብን አፉን፣ የአጐታቸው ልጅ ጃፋር አቡጠሊን፣ የአክስታቸው ልጅ ዘበይር አቡኑልአዋምና ነብዩን እንደ እናት ጡት አጥብተው ያሳደጓቸው እሙአሚን አል ሐበሻ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች አክሱም አካባቢ ነጃሺ ተብሎ በሚታወቀው ጥንታዊ መስኪድ ውስጥ አርፈው በሰላም ኖረዋል።

ከሁሉም በላይ የሚበልጠው ደግሞ የቢላል ታሪክ ነው። ቢላል ቤተሰቦቹ ከኢትዮጵያ የሄዱ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው። አንድ ቀን ነብዩ መሐመድ ቢላል በመረዋ ድምፁ ሲዘይር ይሰሙታል። እናም አስጠርተውት ከእርሳቸው ጋር ይሆናል። በኋላም በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብን ለፀሎት የጠራው ቢላል ነው። ትልቅ ጉብታ ላይ ወጥቶ “አላህ ዋክበር” በማለት የእስልምናን ነፃነት ያወጀ፣ ሙስሊሞችን በሙሉ በፀሎት የሰበሰበው ኢትዮጵያዊው ቢላል ነው።

እነዚህን ታሪኰች ስናይ ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ከነብዩ መሐመድ ጋር የነበራቸውን የጠበቀ ግንኙነት እና የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ያደረጉትን ተጋድሎ ያሳያል። እንደሚባለው ከሆነ ቢላል እስልምናን በመቀበል በዓለም ላይ ሦስተኛው ወይም አራተኛው ሰው ነው እየተባለም ይነገራል።

በአጠቃላይ  ሲታይ የእስልምናን ሃይማኖት በማስፋፋትም ሆነ በመቀበል የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እጅግ በጣም ትልቅ ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ብዙ እውቅና ያልተሰጠው እና ጥቅም ላይ ያልዋለ ነው። ለምሳሌ ከእነዚሁ ታሪኮች ተያይዞ ትግራይ ውስጥ ያለው አልነጃሺ መስኪድ እስልምና ሃይማኖት ገና በዓለም ላይ ሲቆረቆር አብሮ የሚጠቀስ ነው። ስለዚህ ቦታው እንደ መካ መዲና ባይሆንም፤ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ግን ቅዱስ ስፍራ ተብሎ የሚጠቀስ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የነብዩ ልጆችና ቤተሰቦች ያረፉበት ከመሆኑም በላይ እስልምና እንዲኖር እንዲበለፅግ፣ ክፉ እንዳይነካው መሸሸጊያና ማቆያ ሆኖ ያገለገለ በመሆኑ ነው።

የነብዩ መሐመድ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ብዙ የሚባልበትም ነው። ለምሳሌ ነብዩ በተለያየ ጊዜ ለኢትዮጵያው ንጉስ ደብዳቤዎችን መላካቸው ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም አያሌ ስጦታዎችን እና እጅ መንሻዎችንም ለግሰዋል። ዶ/ር ሀሰን ሰኢድ ባቀረቡት አንድ ጥናት ላይ እነዚህን የተላኩትን ስጦታዎች ይዘረዝሯቸዋል። እነዚህም ጥቁር ሙሉ ልብስ፣ የወርቅ ቀለበት፣ የአበሻ ፈርጥ ያለበት ሦስት እንካሴዎች፣ ሽቶ፣ የአበሻ በቅሎዎች እና ሌሎችም ይገኛሉ። እነዚህን ቅርሶች በደንብ መመርመርና ማጥናት ይጠበቅብናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእስልምና ሃይማኖት መንፈሳዊም ሆኑ ቁሳዊ ቅርሶች ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘታቸው ሀገሪቱም ሆነች ምዕመኑ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ዘመናት እየከነፉ ነው።

ለምሳሌ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተመሠረቱ የእስልምና ተቋማት በራሳቸው ታሪካዊ ናቸው። ከብሔረሰቦቻችን መካከል የአርጐባውን፣ የሐረሪውን፣ የቤኒሻንጉሉን፣ የአፋሩን፣ የሱማሌውን እና የኦሮሞውን እስልምና እና እሱን ተከትሎ ያለውን ባህላዊ አተገባበር ማጥናቱና እንደ ቅርስ ማስፋፋቱ ትልቅ ፋይዳ አለው።

ወደ ሐረርና አካባቢዋ ስንሄድ የሐረሪዎችን እና የሐረር ኦሮሞዎችን የጋራ የሆነ እስላማዊ ቅርስ እናገኛለን። የአያሌ መስኪዶች ደብር የሆነችው ሐረር እስልምናን ከተቀበለች ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ሼህ አባድር እና ተከታዮቻቸው የሐረርን ምድር ከረገጡባት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ አያሌ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ‘አሹራ’ ተብሎ የሚታወቀው እስላማዊ በዓል በሐረር ውስጥ በተለየ መልኩ ይከበራል። ይህም ጅቦችን ገንፎ በማብላትና ከጅቦች ጋር ሠላማዊ ኑሮ ከመመስረት ጋር የተገናኘ ልዩ የአካባቢር ስርዓት አለው። ይሄ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙስሊሞች ባህላዊ ቅርስ ነው።

ወደ ወሎ ስንጓዝ ደግሞ መንዙማው ልብን ውክክ እያደረገ በሚንቆረቆረው የወለዬዎች ድምፅና ምርቃት ታጅቦ ይቀርባል። በሙዚቃው ዓለም ይሄ ሌላኛው መንፈሣዊ ስልት ነው። የወለዬዎች የሆነው ይህ ሙዚቃዊ ስልት ብዙ ሊባልለት የሚችል ነው። ዓለም አቀፋዊቷ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ይህንን የመንዙማ የሙዚቃ ስልት ወስዳ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ ዘፈኖቿን ሠርታበታለች።

ከመንዙማው ባልተናነሰ የድሬ ሼህ ሁሴን ታሪክም አንዱ አካል ነው። ወደ ድሬ ሼህ ሁሴን ስንጓዝ ግጥምና ዜማ አውራጆች ከልዩ ልዩ ቦታዎች እየመጡ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚያከብሩበት ስርዓት በእስልምና ሃይማኖታችን ውስጥ የሚገኝ ቅርስ ነው።

ወደ ባሌ ስንጓዝም የሶፍ ዑመር ዋሻ አካባቢ የሚደረጉ ባህላዊ ድርጊቶች እና ክብረበዓሎች ሌላኛው ገፅታችን ናቸው። በዚህ ቦታ ላይም ሶፍ ዑመር የተባሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ እና ቅዱስ የሚባሉ ሊቅ በስፍራው ይኖሩ ነበር። የእኚህን ሰው ገድል ለማድነቅ እና ፈጣሪያቸውን ለማመስገን በየዓመቱ አያሌ የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ስፍራው በማምራት ይገናኛሉ። በጋራ ይፀልያሉ።

ከነዚህ ሌላም በርካታ እስላማዊ ቅርሶች በሐገራችን ውስጥ አሉ። ሁሉንም መጠቃቀስ ባንችልም እነዚህ ይበቁናል። ግን ሳይጠቀስ የማያልፈው ደግሞ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ባህላዊ አለባበሳቸውም ቅርስ ነውና መጠናት እንዳለበት ዶ/ር ሐሰን ሰኢድ ይመክራሉ።

በ2004 ዓ.ም በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን አማካይነት በታተመው ቅርስ በተሰኘው መጽሔት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ክፍል የዓረብኛ ንዑስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ሰዒድ አብደላ “ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ የኢትዮጵያ እስላማዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች” በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አቅርበው ነበር። በዚህም ጥናታቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡትን የእስልምና ሃይማኖት መፃህፍት ጠቅሰዋል።

ከነዚህ መፃህፍት መካከልም ከዛሬ 700 ዓመታት በፊት የተፃፈውን፣ ሺሃቡዲን ዓብዱ አልቃድር (ዓረብ ፈቂህ) የአሕመድ ግራኝ መዋዕለ ዜና ፀሐፊው “ፋቱህ ዓል ሐበሻ” በሚል ርዕስ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፃፈው፣ ዳውድ አቡ በከር እ.ኤ.አ. በ1818 አካባቢ የፃፏቸው በርካታ እስላማዊ መፃህፍት፣ ቡሽራ መሐመድ የተባሉ ሊቅ በ1863 እ.ኤ.አ የፃፏቸውን ኢትዮጵያዊ መፃህፍቶች፣ በ1881 እ.ኤ.አ መሐመድ ጀማል አደን አልዓሊ (አባ ወልዬ) በድርሰት ስራዎቻችው አያሌ ነገሮችን መፃፋቸው ተገልጿል። ሑሴን ሐቢብ (ባሆች) እ.ኤ.አ በ1916 ዓ.ም ከሃይማኖት አባትነታቸው በላይ በርካታ መፃህፍትን አዘጋጅተዋል።

ሐጂ ጃዕፈር በዓረብኛና በአማርኛ ቋንቋ እ.ኤ.አ 1936 አካባቢ መፃፋቸው እና ሸምሰዲን መሐመድ እ.ኤ.አ 1924፣ ሰኢድ ኢብራሂም ያሲን (ጫሎች) በ1940ዎቹ የፃፏቸውና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም ሆነ መንግስት እንዲሁም የቅርስ ወዳጆች የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የማስተዋወቅና የመጠበቅ ተግባር ይጠበቅባቸዋል።

                                                            መልካም የረመዳን ጾም - ረመዳን ከሪም

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15521 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1047 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us