እስኪ እንገጣጠም

Wednesday, 14 June 2017 12:42

 

በጥበቡ በለጠ

“ኢትዮጵያ የገጣሚያን ምድር ነች” ይላሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅሁፍ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ። ጉዳዩን ሲተነትኑትም እዚህ ሀገር የተማረውም ያልተማረውም ገጣሚ ነው። የተማረው የጠረጴዛና የወንበር ላይ ገጣሚ ነው። ቁጭ ብሎ፣ አስቦ፣ ሀሳብ አመንጭቶ ይፅፋል። ያልተማረው ደግሞ የቃል ግጥሞችን በመሸታ ቤት ላዝማሪ በመስጠት፣ በሠርግ፣ በለቅሶ፣ በደቦ፣ በስደት ወዘተ. ለዛቸው የማይጠገቡ ግጥሞችን ሲደረድር ይታያል። እናም ግጥም የዚህች ሀገር ሀብት ነው ባይ ናቸው ዶ/ር ፈቃደ።

በርግጥ ትክክለኛ አባባል ነው። ግጥም በተለይም አንድ የሚያስጨንቅና የታመቀ ሀሳብ ስሜትን ሲፈታተን ፈንቅሎ የሚወጣ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ። ለምሳሌ በመሸታ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው ለአዝማሪው ‘ተቀበል!' በማለት ሁለትና ሦስት ስንኞችን የሚሰነዝሩ ሰዎች አንድ የውስጥ ስሜታቸውን የሚያንፀባርቁበት አጋጣሚ ነው። በፍ/ቤት የገተራቸውን ለመሸንቆጥ፣ ወይም ኰማሪቷን በመፈለግ፣ አልያም ጠላቴ ነው ብለው ለሚያስቡት ሰው.... ብቻ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ።

ዛሬ ደግሞ ግጥሞች በመፃህፍት መልክ እየታተሙ በመውጣት እስከ ቅርብ ጊዜ ያልታየውን የዚህን ዘርፍ እንቅስቃሴ የትየለሌ እያደረሱት ነው። አነሰም በዛ ግጥም ይፃፋል ይታተማል። በየግጥም ምሽቱና ግጥም በማለዳ በተሰኙ መድረኮችም ግጥም ይነበባል።

በዚሁ ዘመን የሚታዩ ግጥሞች ባህሪዎቻቸው ደግሞ ካለፉት ዘመናት የተለየ ነው። ይህም አጫጭር ግጥሞች በስፋት የሚታዩበት ሁኔታ ይስተዋላል። ለምን አጠሩ? ይሄ ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናትና ትንታኔ የሚጠይቅ ነው። ለጨዋታ ያህል ግን ሲነሳ ደግሞ የግጥሙ ርዕሰ ጉዳይ ራሱ ለእጥረትና ለርዝመቱ እንደ አንድ አብይ ምክንያት ይቆጠራል የሚሉም አሉ። ለምሳሌ አባይ፣ አዋሽ ብለን ብንጀምር መቆሚያችን የት ነው? እንደ ወንዙ ርዝማኔ እና ስፋት የግጥሙም ሀሳብ ይረዝማል ይሰፋል።

ታላላቅ ርዕሰ ጉዳዮች ታላላቅ ገለፃና ሰፊ ሃሳብ ጋር ይንሸራሸራሉ በማለት ሲገልፁ፣ እነዚህ ሰዎች ደግሞ አጭሩን ግጥም የሀሳብ እጥረት አለበት እስከ ማለት አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ።

በሌላኛው ፅንፍ ያለው ተከራካሪ ደግሞ ግጥም ረዝሞ ሲንዛዛ ሳይሆን ትልልቅ ሃሳቦችን ሰብስቦ በአጭሩ የሚያቀርብ ነው። ግጥም ማለት አጭር ሲሆን ነው ብለው በተለይም ለአሁን ዘመን የግጥም አብዮት ውዳሴ ይሰጣሉ።

ከሁለቱም ሀሳቦች ሣይሆኑ መሀል ላይ ሆነው ከማንም ጋር የማይቀያየሙት አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ ግጥም ስላጠረም ስለረዘመም አይደለም የብቃትና የጥራት ደረጃው የሚለካው ባይ ናቸው። ረጅሙ ግጥም ወይ ውብ አልያም አስቀያሚም ሊሆን ይችላል። አጭሩም እንደዚያው ነው ባይ ናቸው።

በርግጥ ግጥም ተሰጥኦንም የቋንቋ ሀብታምነትንም ይጠይቃል። ገጣሚው ስለሚፅፍበት ቋንቋ ምን ያህል ቃላቱን፣ ስርዓቱን፣ ቀለሙን ወዘተ. ያውቃል? የሚሉት ነገሮች መነሳት አለባቸው።

መነሻ መሠረቱን የቋንቋው እውቀት ላይ አድርጐ የተነሳ ገጣሚ መንገዱ ሁሌ ቀና እየሆነለትእንደሚሄድ ይነገራል። ስራውንም ያቀላጥፍለታል ተብሎ ይታመናል። ገጣሚነት ከዚህ ሌላ እውቀት ነው። ሰፊ ንባብ፣ ማንኛውንም ነገር ለማወቅ “መቆፈርን” የሚጠይቅ፣ ማህበረሰቡን በጥልቀት ማወቅ፣ ባህልን፣ ወግን፣ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን... በሰፊው ለመገንዘብ የሚችልና ሁሉም ነገር እጁ ላይ እንዲኖር ማድረግ መቻል አለበት። ከእንዲህ አይነት ሰው ነው ጥልቅና ሰፋ ያለ ሀሳብ ያለው ግጥም ማግኘት የሚቻለው።

ገጣሚያን ስራቸው የተቃና እንዲሆንላቸው በማሰብ አያሌ የቋንቋ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት ጥናቶች አቅርበዋል። መንግሥቱ ለማ፣ ዓለማየሁ ሞገስ፣ ዜና ማርቆስ እንዳለው፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ከዚህ ከዘመንተኞቹ ደግሞ ሳሙኤል አዳል፣ አበራ ለማ፣ ብርሃኑ ገበየሁ ይጠቀሳሉ። ግጥም ላይ ብዙ ነገር ተናግረዋል ፅፈዋል።

በተለይም የአንድ ገጣሚን ልዩ ብቃት የሚወስኑት በማለት የሚያስቀምጧቸው የቃላት አጠቃቀምን (Diction)፣ የዘይቤ አጠቃቀምን (Figurative Language)፣ የግጥሙ ዜማዊነትና (Rhythm)፣ አሰኛኘት (Versification) የመሳሰሉት በገጣሚው ዘንድ በሰፊው ከታወቁ 'አውቆ ገጣሚ' የሚያሰኙት ነጥቦች እንደሆኑ ይገልፃሉ። ወር በገባ የመጀመሪያ ረቡእ ግጥሞቻቸውን ይዘው የሚቀርቡት ፖየቲክ ጃዞች የዚህ መልካም ግጥም አርአያዎች ናቸው። የግጥም አብዮት እያካሄዱ የሚገኙ ናቸው።

የቃላት ምርጫ ሲባል ተደጋግሞ እንደሚነገረው እምቅና ሃይለኛ ቃላት በግጥም ውስጥ ይግቡ የሚለው ሀሳብ ዛሬ ዛሬ ውድቅ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱም ቃላት በተገቢው ቦታቸው ላይ እስከ ገቡ ድረስ ኃይለኛና እምቅ ናቸው። ጉዳዩ ትክክለኛውን ቦታቸውን አውቆ መርጦ የማስገባቱ ስራ ላይ ገጣሚው መጠንቀቅ ያለበት።

በርግጥ አንዳንድ ገጣሚዎች ቃላትን ይፈጥራሉ። ለቦታው ለሁኔታው የሚያመቻቸውን ገለፃ ለመጠቀም ሲሉ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያሉ ሰዎች በተለይም ጥምር ቃላትን (Compound Word) ይመሰርታሉ። ፀጋዬ ከአማርኛና ከኦሮምኛ እያደረገ ያጣመራቸው ቃላት ለቋንቋው እድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ ወደር አይገኝለትም። እናም ገጣሚ ቃላት ተጠቃሚ ብቻ ሣይሆን ፈጣሪም ነው።

ገጣሚያን የቃላትንም እማሬያዊእና ፍካሬያዊ ፍቺ (Denotative and Connotative) ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ ‘ውሻ'  የሚለው ቃል በብዙ ቦታዎች ላይ ሲገባ ብዙ አይነት ፍቺ ይኖረዋል። ይህም አንደኛው የቤት እንስሳ የሆነውን የሰው ልጅ በጣም የሚቀርበውን እንስሳ ማለታችን ሲሆን፤ ሁለተኛው ወይም ፍካሬያዊው ፍቺ ደግሞ ስድብ ነው። ልክስክስ እንደማለት ነው። በሌላ መልክ ደግሞ እናቶቻችን “የኔ ውሻ” ይሉናል። ይህም ‘የኔ ፍቅር' ማለታቸው ነው። ስለዚህ የዘመኑ ገጣሚዎች ይህን ክፍልም መመርመር ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ሌላ ግጥምን ዘመን ዘለልና አይረሴ ከሚያደርጉት ባህርያት አንዱ ዘይቤያዊ አጠቃቀም ነው። በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በርካታ ዘይቤያዊ አጠቃቀሞች አሉ። ገጣሚያን እነዚህን የዘይቤ አይነቶች ቢያውቋቸው ስራዎቻቸው የበለጠ ማራኪነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ። ምክንያቱም ዘይቤዎች በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ ምስል በመከሰት የአይረሴነትን ሁኔታ ይፈጥራሉና።

ግጥም ከሰው ልጅ አእምሮ የራቀን ነገር ወይም ረቂቅ ነገርን ማሳያ ስለሆነ ዘይቤ ደግሞ ለዚህ አይነቱ ነገር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል። ረቂቁን አጉልቶ ማሳየት፣ በሀሳብ አድማስን ዘልቆ መሄድን ሁሉ የሚፈጥርልን ነው።

ከነዚህ የዘይቤ አይነቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ዳሰስ አድርገን እንለፍ።

1.ተነፃፃሪ ዘይቤ (Simile)

ይህ የዘይቤ አይነት አንድን ነገር ከሌላ ነገር ጋር በማነፃፀር በማወዳደር የሚያቀርብ ነው። አንዳንዶች አነፃፃሪ ዘይቤ ይሉታል። ይህን ዘይቤ በስፋት ተጠቅሞበት የተዋጣለት ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን ነው።

እንደ ፍካሬ ኢየሱስ ቃል፣ እንደ ሙታን የግዞት ህግ፣ ተውተብትቦ ተጥለፍልፎ፣ ተቆላልፎ እንደ ዛር ድግ አነፃፃሪው ቃል እንደ የሚለው ነው።

2.ተለዋጭ ዘይቤ (Metaphor)

ይህ ዘይቤ ገጣሚው አንድን መልዕክት ከሌላ ነገር ጋር በሚያነፃፅርበት ጊዜ፣ ‘እንደ'፣ ‘ይመስላል'፣ ‘ያህል' የሚሉትን ማነፃፀሪያዎች ትቶ አንዱን ካንዱ ጋር ሲያመሳስል የተፈለገውን ምስል ማምጣት እንዲችል የሚያደርገው ነው። አንድ ያልታወቀ ገጣሚ እንዲህ ብሏል፡-

እግረ-ኰሸሸላ፣ ወገበ ግራር

ጨርቄን ጨረሰችው፣ ባንድ ቀን አዳር።

3.ሞረሽ፣ ማነሔ፣ እንቶኔ (Apostrophe)

ይሄ የዘይቤ አይነት የማይናገርን፣ የማይሰማን ግዑዝ አካል ማናገር ነው። ለምሳሌ የግርማ ታደሰ ተናገር አንተ ሀውልት የሚለው ግጥም፣ ተጠቃሽ ነው።

 

4.  ኩሸት (Hyperbole) 

የዚህ የዘይቤ ተፈጥሮ ከመጠን በላይ አጋኖ መናገርን ያሳያል። አንድ ገጣሚ እንዲህ ሲል አስቀምጧል።

እንቁ ወርቅና አልማዝ ተነጥፏል ለግርሽ

የህይወት ምንጭ ነው ገፅሽ ጉተናሽ

አንጋጠው ያዩሻል ጐረቤቶችሽ።

 

5.ምፀት (Irony)

ይሄ ዘይቤ የቀጥታ ትርጉም የለውም። ፍቺው የተነገረውን ነገር በተቃራራኒው ማሰብ ነው። የፀጋዬ ገ/መድህን “እንዳይነግርህ አንዳች እውነት” የሚለውን ግጥም ማንበብ ይጠቅማል።

ደንስ ጐበዝ ደንስ ጀግና

ክራቫትክን አውልቅና

ሀሳብክን ልቀቀውና

ኮትህን ሸሚዝክን ጣልና

ርገጥ፣ ጨፍር፣ ደንስ ጀግና

6.አያዎ (Paradox)

ይህ ዘይቤ አንድን ነገር ተፅፎ ወይም ተነግሮ ስናነብ ወይም ስንሰማ ልክ ነው ብለን ተቀብለን፣ እንደገና ደግሞ እንዴት ሊሆን ይችላል በማለት ሀሳባችንን ስንቀይር ስናወላውል የምንታይበት ነው። ኢብሳ ጉተማ እንዲህ ብሏል።

ገና ያልተነካች፣ ድንግል መሬትን

ማን ህጓን ይወስዳል፣ ሰዎች ከሌለን?

 

7.ድምፅ ቀድ (Onomatopoeia)

ይህ ዘይቤ በተለይም ከተፈጥሮ ድምፆችና ድርጊቶች ኮርጀን የምንጠቀምበት ነው። ለምሳሌ በሩ ኳ! ኳ! ኳ! አለ። የበር ድምፅን ነው። ከ.... ከከ.... ከከ ብሎ ሳቀ። እነዚህ ከተፈጥሮ ድምፆች የምንኮርጃቸው ናቸው። በዚህ የሚጠቀሱት የሀገራችን ገጣሚ መታፈሪያ ፍሬው ናቸው።

8.  ተምሳሌታዊ (Symbolic) 

ተምሳሌታዊ ዘይቤ ነገሮችን በውክልና ስንገልፃቸው ነው። ለምሳሌ ወንዝን እንደ ትውልድ እንደ ህዝብ መቁጠር፣ ባንዲራን ለሀገር፣ ተራራን ለስልጣን፣ እባብን ለተንኮል ወዘተ. አድርጐ መጠቀምን ያሳያል። በርግጥ ተምሳሌታዊ ዘይቤ ሁለት አይነት ነው። አንደኛው አለማቀፋዊ (Universal Symbolism) የሚባል አለ። በሁሉም ሀገር ተመሳሳይ የሆነ ነው። ለምሳሌ ባንዲራ። ሁለተኛ አካባቢያዊ (Local Symbolism)  የሚባለው ነው። በተወሰነ ቦታ እና አካባቢ ላይ ብቻ የሚታመንበት ነው። ለምሳሌ በህንድ ሀገር እባብ የጥሩነት መግለጫ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ የመሠሪነትና የተንኮል መሆኑን ልብ ማለት ይጠቅማል።

9.ሰውኛ (Personification)

ይህ ዘይቤ ህይወት የሌላቸውን ነገሮች እንደሰው አድርጐ ማቅረብን ያሳያል።

ከድሀውም ድሀ - ከቱጃሩም ቱጃር

እንደሁሉም ሆና - ሁሉንም የምትኖር

በየጉራንጉሩ - በየበራፉ ላይ

ኪዮስክ ትንሿ ቤት - የአፍንጫ ስር ተባይ።

የዚህ ግጥም ደራሲ አስራት ዳምጠው ነው። ስራውን ያስተዋውቀን ገጣሚ አበራ ለማ ኪዮስክ ድሀም፣ ቱጃርም ሰው ሆና መቅረቧን ገልጿል።

ባጠቃለይ በዘመናችን በሚያስደስት መልኩ የግጥም ስራዎቻቸውን ይዘው የሚቀርቡ ወጣቶችን ከግጥሞቻቸው ጐን ለጐን ጠለቅ እያሉ በተለይም የአማርኛ ቋንቋ የአገጣጠም ስልቶች፣ ቀለሞችን፣ ዜማዎችን፣ የጥንቶቹ ምን ገጠሙ? የኛ ከእነሱ በምን ይለያል የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ቢያጠኑ ጥሩ ነው እላለሁ። ዛሬ የተያያዙት ጐዳና የፈካ እንዲሆን በሁሉም አቅጣጫ ቆፋሪዎች ይሁኑ።

ይምረጡ
(30 ሰዎች መርጠዋል)
17182 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 815 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us