ከወራሪዎች ጋር የተናነቁ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን በጥቂቱ

Wednesday, 03 May 2017 12:32

 

በጥበቡ በለጠ

ከነገ በስቲያ ሚያዚያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም የአርበኞች ቀንን እናከብራለን። ዛሬ እኛ እንድንኖር ስንቶች ወድቀውልናል። ሕይወታቸውን ሰጥተውልናል። ሁሉንም መዘርዘር አይቻልም። ግን ጐላ ጐላ የሚሉትን የጥበብ ሠዎችን ብቻ ለመቃኘት እሞክራለሁ።

በአማርኛ ሥነ-ጽኁፍ ውስጥ ታላላቅ የሚባሉ ደራሲያን ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል። እስኪ እነሱን ደግሞ ጥቂት እንዘክራቸው።

ፋሽስት ኢጣሊያ በ1929 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር በሐገሪቱ ኢኰኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥራለች። በአምስት ዓመታት ቆይታዋም ተዘርዝሮ የማያልቅ ኢሰብአዊ ድርጊት በዜጐች ላይ ፈፅማለች። አያሌ የኢትዮጵያ የፅሁፍ ሠነዶችና ታሪኰችን አውድማለች። የሥነ-ፅሁፍ ዘርፉን ብቻ እንኳን ስንቃኝ ፋሽስት ኢጣሊያ በርካታ የኢትዮጵያ ደራሲያን እና የጥበብ ሰዎች እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱ እና እንዲሰቃዩ አድርጋለች። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ለፋሽስት ኢጣሊያ ያደሩ የኢትዮጵያ ደራሲዎች፣ ባለቅሬዎችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ነበሩ። በዛሬው ፅሁፌ ወራሪዋን ጣሊያንን የተፋለሙ እና የደገፉ የጥበብ ሰዎቻችንን እቃኛለሁ።

ተመስገን ገብሬ

ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ከመውረራቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ወረራው አይቀሬ መሆኑን የተገነዘቡ ታላላቅ ደራሲያን ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ተመስገን ገብሬ ነበር። ጋዜጠኛ እና ደራሲ የነበረው ተመስገን ገብሬ፣ በ1928 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ሊወሩ ነው በማለት በየአደባባዩ ህዝብ እየሰበሰበ ንግግር ያደርግ ነበር። ኢትዮጵያዊያን በቅርቡ የሚመጣባቸው ጠላት ምን ያህል የተደራጀ እና የተዘጋጀ እንደሆነ ያስረዳቸው ነበር። ይህ ግዙፍ የኢጣሊያ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ህዝቡ እንዴት መከላከል እና ሀገሩን መጠበቅ እንዳለበት ተመስገን ገብሬ በየአደባባዩ ይናገር ነበር። በተለይ ደግሞ ዛሬ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተብሎ በሚጠራው እና በዚያን ዘመን የሀገር ፍቅር ማኅበር ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ከሌሎችም ጓደኞቹ ጋር በመሆን ህዝቡን ያስተምር ነበር።

ፋሽስት ኢጣሊያኖችም አዲስ አበባን በተቆጣጠሩበት ወቅት ቅድሚያ ሰጥተው ከሚያድኗቸው ሰዎች መካከል አንዱ ተመስገን ገብሬ ነበር። ተመስገን ከኢጣሊያኖች ራሱን እየሸሸገ በርካታ የአርበኝነት ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ለምሳሌ ለአርበኞች በከተማ ውስጥ ያለውን መረጃ ያቀብል ነበር። ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በጣሊያኖች እንዳይወድሙ ከእንግሊዞች ጋር ሆኖ ወደ ለንደን እንዲሄዱ አድርጓል። ከነዚህም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተተረጐመው ግዙፍ የብራና መፅሐፍ ይገኛል። ተመስገን በአደራ መልክ ከአገሩ ያስወጣው ይሄው ብራና ዛሬም ድረስ እንግሊዝ ውስጥ ይገኛል።

ከዚህ በተረፈም ተመስገን ገብሬ በየካቲት 12 ጭፍጨፋ ወቅት እጅግ ዘግናኝ ድርጊቶችን ያየ ሲሆን፤ እሱ ራሱም እስረኛ ሆኖ በተአምር አምልጦ ወደ ሱዳን ይሰደዳል። እዚያም ሆኖ ለንደን ውስጥ ካሉት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘንድ መልዕክት እየተቀበለ ለአርበኞች ይልካል። ከአርበኞች ተቀብሎ ለንጉሱም ይልካል። በስደት ያሉትን ኢትዮጵያዊያንን ሱዳን ውስጥ ያስተምር ነበር። “ሊግ ኦፍ ኔሽን” ላይ ጃንሆይ ንግግር ሲያደርጉ በርካታ መረጃዎችን ፅፎ የላከላቸው ይኸው አርበኛ ደራሲ ነው።

ተመስገን ገብሬ ኢጣሊያ በሽንፈት ከኢትዮጵያ ምድር ተጠቃላ እንድትወጣ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ አርበኞች አንዱ ነው። ከነፃነት በኋላም ወደ ሀገሩ መጥቶ እጅግ ታዋቂ ጋዜጠኛ እና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያ ነበር። “የኤርትራ ድምፅ” ተብላ የምትታወቅ የመንግስት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። ከዚህ በተረፈም ኤርትራ ከእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር እንድትላቀቅ ከሲልቪያ ፓንክረስት ጋር ሆኖ አያሌ ተግባራትን አከናውኗል።

ተመስገን ገብሬ ጐጃም ውስጥ ደብረማርቆስ ከተማ በ1901 ዓ.ም ተወልዶ፣ በትምህርቱም ከቤተ-ክህነት እስከ ዘመናዊ ት/ቤት ድረስ የተማረ፣ የአዳዲስ አስተሳሰቦች ፈጣሪ የነበረ ደራሲ ነው። በ1941 ዓ.ም በ40 ዓመቱ የተመረዘ ነገር በልቶ ህይወቱ ማለፉ ይነገራል። ተመስገን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ የአጭር ልቦለድ መፅሐፍ እንደሆነች የምትታወቀዋን “የጉለሌው ሰካራም” የምትሰኘዋ መፅሐፍ ደራሲ ነው። ከዚህም ሌላ “ሕይወቴ” በሚል ርዕስ የፃፋትም የህይወት ታሪኩን የምታወሳው እጅግ ተወዳጅ መፅሐፍ እስከ ዛሬ ድረስ ትነበባለች።

መላኩ በያን ለሀገራቸው የሰጡት ሙያዊ ድጋፍ

ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ድግሪ በ1928 ዓ.ም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነው ከመመረቃቸው በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው እያገለገሉ ነበር። የኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካ አሜሪካዊያን ግንኙነት እንዲስፋፋ ብርቱ ትግል አድርገዋል። የተለያዩ ኢትዮጵያዊያንም ወደ ምዕራቡ ዓለም ሄደው ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ እያደረጉ ነበር። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ሁሉንም እቅዶቻቸውን ትተው ወረራው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳትና ውጤትም መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ለአሜሪካዊያንና ለካሪቢያን ዜጐች ያስረዱ ነበር።

በህክምና ከተመረቁ በኋላም ወረራው ሲፈፀም ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ወዲያውም ወደ ኦጋዴን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን የቆሰሉ ወታደሮችን ያክሙ ጀመር። በወቅቱ በጅጅጋ፣ በደገሃቡር እና በጐሬ የተዋጣለት የሕክምና አገልግሎት አበርክተዋል።

እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1935 ዓ.ም ጃንሆይ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሰሜኑ ጦር ግንባር ሲጓዙ ዶ/ር መላኩም ከኦጋዴን ተጠርተው የንጉሱ ልዩ ሐኪም በመሆን ወደ 120ሺ ለሚጠጉ ቁስለኞች ህክምና ሰጥተዋል። በወቅቱ ከኢትዮጵያዊያን በርካታ ሰዎች በመጐዳታቸው የንጉሱም ጦር ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ትዕዛዝ ተላለፈ። እስከዚያው ድረስ ግን ዶ/ር መላኩ የንጉሱ ልዩ ሐኪም፣ አስተርጓሚ፣ ፀሐፊና ቃል አቀባይ ሆነው ይሰሩ ነበር።

አዲስ አበባ እንደገቡም ራስ ካሣ ንጉሱ ከሀገር ወጥተው በወቅቱ “ሊግ ኦፍ ኔሽን” ተብሎ በሚጠራው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤቱታ እንዲያቀርቡ ሀሳብ ሰጡ። ሌሎች ሹማምንት ሀሳቡን ተቃወሙት። ብላታ ታከለ የተባሉ አርበኛ ንጉሱ እዚህ እንደ ቴዎድሮስ በሀገራቸው መዋጋት እንዳለባቸው ተናገሩ። ሌሎች አርበኞች ደግሞ ንጉሱ እንዳይሄዱ ከመንገዳቸው ለማሰናከልም አሴሩ። ዶ/ር መላኩ ግን ምንም ሀሳብ አልሰጡም ነበር።

አፄ ኃይለሥላሴ ወደ አውሮፓ በስደት ሲጓዙ ዶ/ር መላኩም አብረዋቸው ተጓዙ። ንጉሱ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 1936 ዓ.ም በሊግ ኦፍ ኔሽን ታሪካዊውን ንግግር አደረጉ። ሆኖም ከአባል ሀገሮቹ ቀና ምላሽ አላገኙም ነበር። በዚህ ወቅት ቀደም ሲል የንጉሱን ከሀገር መውጣት ይቃወሙ የነበሩት አርበኞች ትክክል እንደነበሩ ዶ/ር መላኩ ተቀበሉ። “የቀረን ተስፋ እዚያው በሀገራችን ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግላችንን ማፋፋም ነው። በዚህም ምክንያት በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች ከጐናችን ይቆማሉ”  ሲሉ ተናገሩ።

በመቀጠልም ዶ/ር መላኩ እ.ኤ.አ በመስከረም 1936 ዓ.ም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው ከእንግሊዝ ሀገር ወጡ። አሜሪካ እንደደረሱም የአውሮፓ ቆይታው ስሜታቸውን ክፉኛ እንደነካው ገልፀዋል። እንግሊዝ ሀገር እያሉ ከታዋቂዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ከኢትዮጵያ አፍቃሪዋ ከሲልቪያ ፓንክረስት እና ከፕሮፌሰር እስታንሊ ዮናስኪ እና ከሌሎች ጥቂት እንግሊዛዊያን በስተቀር ሁሉም ማለት ይቻላል ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን ድል ማድረግ አትችልም የሚል እምነት ነበራቸው ብለዋል።

አሜሪካ እንደደረሱም በእርዳታ ማሰባሰብ ተግባር ላይ ተሰማርተው ለኢትዮጵያ አርበኞች ከፍተኛ ውለታ አበርክተዋል። በርካታ ጥቁር አሜሪካዊያንን በየቀኑ እየሰበሰቡ “እኛ በቅኝ መገዛት የለብንም፣ አርበኞች በዱር በገደል ጠላቶቻችን ከሀገራችን ለቀው እስከሚወጡ ድረስ ይዋጋሉ፤ ጥቁሮች ያሸንፋሉ” በማለት ንግግር ያደርጉ ነበር።

ትግሉን ለማፋፋም የኢትዮጵያ ድምፅ “The Voice of Ethiopia” የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመሩ። በዚህ ጋዜጣ የሀገሪቱን ታሪክ፣ የሕዝቡን ህይወት፣ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልን፣ የነፃነትን ክቡርነት ወዘተ … እየፃፉ ያሰራጩ ነበር። በኋላም “የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን” የተሰኘን ድርጅት አቋቋሙ። በዚህም ድርጅት ጥላ ስር የኢትዮጵያ ወዳጆችና ደጋፊዎች ተሰባሰቡ። ጋርቬይ ይመራው የነበረው “The Universal Negron Improvement Association” አባላትም ይቀላቀሉት ጀመር። የዶ/ር መላኩ በያን እንቅስቃሴ የተባበሩት የአፍሪካ አሜሪካዊያን ማኅበርን መመስረት ነበር። በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና፣ ክብር አግኝተውበታል።

በመካከሉ ግን ጋርቬይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከጥቁሮች ነጮችን ይወዳሉ እያለ መናገር ጀመረ። በዚህ ጊዜ ከዶ/ር መላኩ በያን ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ። ይህ የጋርቬይ ንግግር ፍፁም ሀሰት እንደሆነ ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን እያቀረቡ ለደጋፊዎቻቸው አስረዱ። ገለፃቸውም አሳማኝ ነበር።

ዶ/ር መላኩ ከባለቤታቸው ዶሮቲ ጋር በመሆን በሚያደርጉት ትግል የአያሌ ጥቁር አሜሪካዊያንን ድጋፍ አግኝተዋል። “ለነፃነት መፋለሚያው አሁን ነው” ተስፋፊዎችን በኅብረት እንቃወም። ሊግ ኦፍ ኔሽንን እናውግዝ። ጣሊያንን እናውግዝ። ነፃ የጥቁሮች ሀገር ይኑር እያሉ በየተሰባሰቡበት እየተናገሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ተከታዮች አፍርተዋል።

የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ታጋይ፣ የነፃነት ተሟጋች፣ የጥቁር ኅብረት ናፋቂ የሆኑት ዶ/ር መላኩ በያን ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ልዕልና ሲሉ በየስፍራው እንደዋተቱ በኒውዮርክ ከተማ እ.ኤ.አ ግንቦት 4 ቀን 1940 ዓ.ም ከዚህች ዓለም በሞት ተለዩ።

ወትሮም ሲናፍቁት የነበረውና ሲታገሉለት የኖሩት የፋሽስቶችን ውድቀት ሳያዩ በማለፋቸው ብዙዎች ይቆጫሉ። ጣሊያኖች ድል ተደርገው ሊወጡ አንድ ዓመት ሲቀራቸው ነበር ያረፉት።

ከጋርቬይ ጋርም አንድ የሚያደርጋቸው ሁለቱም የአፍሪካ ወዳጆች ሁለቱም የዘር መድልዎን ተቃዋሚዎች ጭቆናን በደልን ታጋዮች በመሆናቸው ለነፃነት በተደረገው ትግል ሁሉ ሲታወሱ ይኖራሉ።

በአገራችን የዶ/ር መላኩ በያን ስም የሚያስጠራ ጐዳናም ሆነ ሐውልት የለም። ይሁንና ስድስት ኪሎ በሚገኘው የካቲት 12 ሆስፒታል ውስጥ በዶ/ር መላኩ በያን የተሰየመ የህክምና ማዕከል መኖሩን ምን ያህሎቻችን እናውቅ ይሆን?    

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ

በ1887 ዓ.ም ጐጃም ውስጥ ደብረኤልያስ በተባለ ቦታ የተወለደው ዮፍታሔ ንጉሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትርን እና መዝሙርን በማስተማር እና በማስፋፋት ግንባር ቀደም ከያኒ ሆኖ ይጠራል።

ይህ የኪነ-ጥበብ ሊቅ ልክ እንደ ተመስገን ገብሬ ሁሉ ህዝብ እየሰበሰበ ከኢጣሊያ ወረራ ህዝቡ እንዴት መከላከል እንዳለበት ያስተምር ነበር። ጣሊያኖች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ በእጅጉ ከሚፈለጉ ሠዎች መካከል አንዱ እርሱ ነበር።

ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ

በአርበኝነቱ ታጥቆ ጠላት ያስወገደ

ንጉሱን አገሩን ክብሩን የወደደ

ነፃነቱን ይዞ መልካም ተራመደ።

ገናናው ክብራችን ሰንደቅ አላማችን፣

እጅግ ያኰራሻል አርበኝነታችን።

እያለ መዝሙር ያዘምር ነበር።

ዮፍታሔ በኢትዮጵያዊያን ባንዳዎች ጠቋሚነት ጣሊያኖች ሊይዙት እቤቱ ሲመጡ ራሱን ቀይሮ ቄስ መስሎ ከአዲስ አበባ ጠፍቶ በዱከም በኩል አድርጐ ከአርበኞች ጋር ተቀላቀለ። ከዚያም ወደ ሱዳን ተሰደደ። በአምስት ዓመቱ የጦርነት ወቅት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በስለላ መልክ እራሱን ቀይሮ እየመጣ ለአርበኞች ልዩ ልዩ ነገር እያቀበለ ይመለስ ነበር። ከዚህም ሌላ ልዩ ልዩ መቀስቀሻ ግጥሞችን እና ቅኔዎችን እየፃፈ በየጦር አውድማው ይልክ ነበር። የፋሽስቶች ግብዐተ መሬት እስከሚጠናቀቅ ለሀገሩ ብዙ የከፈለ ከያኒ ነው።

ዮፍታሔ ንጉሴ በ1933 ዓ.ም ጣሊያኖች ድል ሲመቱ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የጉዞ ማስታወሻ ፀሐፊ ሆኖ ከሱዳን እስከ አዲስ አበባ ድረስ መጥቷል። ከዚያም ግሩም የሆነ የፅሁፍ ሠነድ አዘጋጅቶ አውጥቷል።

ዮፍታሔ ንጉሴ በቴአትር ዘርፉ ከሚታወቁለት ስራዎቹ መካከል “አፋጀሽኝ”፣ “እያዩ ማዘን”፣ “የሆድ አምላኩ ቅጣት”፣ “ምስክር”፣ “እርበተ ፀሐይ”፣ “ታላቁ ዳኛ”፣ “የሕዝብ ፀፀት” እና ሌሎችም ይገኛሉ። በመዝሙሩም በኩል ቢሆን በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ብሔራዊ መዝሙር የፃፈ ታላቅ ሀገር ወዳድ ከያኒ ነበር። በ1935 ዓ.ም ደግሞ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ም/ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል።

ዮፍታሄ ንጉሴ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ቀን ስራውን በሰላም ሲሰራ ውሎ፣ ማታ እቤቱ ገብቶ ተኛ። ጠዋት ላይ ግን አልጋው ላይ ሞቶ ተገኘ። የዚህ ታላቅ አርበኛ እና ደራሲ አሟሟትም ምስጢር ሆኖ እስከ አሁን ድረስ አለ።

ሐዲስ አለማየሁ

በ1902 ዓ.ም ጐጃም ውስጥ ደብረማርቆስ አውራጃ፣ ጐዛምን ወረዳ፣ እንዶዳም ኪዳነምህረት በተባለች ስፍራ የተወለዱት ታላቁ ደራሲ፣ አርበኛና ዲፕሎማት ሐዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ እጅግ ጐልተው የሚጠሩ ናቸው። እኚህ ደራሲ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት አያሌ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።

ጣሊያን ኢትዮጵያ ስትወር ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ከራስ እምሩ ኃይለስላሴ ጦር ጋር በመሆን ፋሽስቶችን በልዩ ልዩ አውደ ውጊያዎች ሲፋለሙ ቆይተዋል። በመጨረሻም ተማርከው በፋሽስቶች እጅ ይወድቃሉ። ከዚያም ወደ ጣሊያን ሀገር ሄደው እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው። ሊፓሪ /Lipari/ ወደተባለ ደሴት ተወሰዱ። ቀጥሎም በሳንባ ምች ስለታመሙ ወደ ሉንጐ ቡክ ወደተሰኘ ስፍራ ተዘዋወሩ። እዚያ ደግሞ እንደ ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት ያለ ታላቅ ደራሲም ታስሯል።

በአጠቃላይ ሐዲስ ዓለማየሁ በኢጣሊያ እስር ቤት ወደ ሰባት ዓመታት ታሰሩ። ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ወረራ ነፃ መውጣቷን እስር ቤት ሆነው ሰሙ። በእሰርም ቢሆኑ የሀገራቸው ነፃ መውጣት አስደሰታቸው። ከነፃነት በኋላ ማለትም በ1936 ዓ.ም በእንግሊዞች እና በሌሎች ጦረኞች ትግል ከእስር ቤት ወጥተው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ መጥተዋል።

ሐዲስ ዓለማየሁ ከነፃነት በኋላም በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ከ1943 ዓ.ም እስከ 1953 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር፣ ከዚያም በብሪታኒያ በኔዘርላንድስ እና በልዩ ልዩ ቦታዎች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ በሀገራቸውም ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ከጃንሆይ ስር ሆነው በሚኒስትርነት አገልግለዋል።

ሐዲስ ዓለማየሁ በድርሰቱም መስክ “ተረት ተረት የመስረት (1948)”፣ “የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም (1948)”፣ “ፍቅር እስከ መቃብር (1958)”፣ “ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል (1966)”፣ ወንጀለኛው ዳኛ (1974)፣ “የልምዣት (1980)”፣ “ትዝታ (1985)” የተሰኙ መፃህፍትን አበርክተዋል። ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅትም በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ተሸላሚ ናቸው። በ1992 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል። ሐዲስ ዓለማየሁ በ1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት

ጥቋቁር አናብስት /Black Lions/ በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥ ኖርዌጂያዊው ሞልቬር፣ ግርማቸው ተ/ሃዋርያት እ.ኤ.አ ኖቬምበር 21 ቀን 1915 ዓ.ም ሐረርጌ ውስጥ ሂርና ተብላ በምትታወቀው ስፍራ መወለዳቸውን ይገልፃል። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ዓለም ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት እኚህ ታላቅ ደራሲ፣ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ብዙ ስቃይ አሳልፈዋል።

ግርማቸው ተ/ሃዋርያት የማይጨው ጦርነት ሲደረግ ጃንሆይን ተከትለው ዘምተው ነበር። በኋላ ከልዑል አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለስላሴ ጋር ሆነው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል። ኢጣሊያ አዲስ አበባን በተቆጣጠረችበት ወቅት እርሳቸው ወደ ጅቡቲ ተሰደዱ። እዚያም አየሩ አልስማማ ስላላቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። እርሳቸው በሚመለሱበት ወቅት ደግሞ ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ ቦምብ የወረወሩበት ጊዜ በመሆኑ ግርማቸውም በቁጥጥር ስር ዋሉ። ጣሊያኖቹም ግርማቸውን ወደ ኢጣሊያ አገር ወስደው አሰሯቸው። አሲናራ በተባለች ደሴት ላይ ከታሰሩ በኋላ ሐዲስ ዓለማየሁ እና ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ወደታሰሩበት ሊፕሪ ደሴት ተዘዋወሩ። ከዚያም አነስተኛ መንደር ወደሆነችው ካላቡሪያ ተሸጋገሩ። በአጠቃላይ ለሰባት ዓመታት ኢጣሊያ ውስጥ ታሰሩ።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ ሲል በጄኔራል ዊልሰን የሚመራ የእንግሊዝ ጦር እነ ግርማቸው ያሉበትን ስፍራ ይቆጣጠራል። እናም እነ ግርማቸው ተ/ሃዋርያት ከሰባት ዓመታት እስር በኋላ በ1935 ዓ.ም ተፈቱ። በመጀመሪያ ካይሮ፣ ከዚያም ምፅዋ፣ ቀጥሎ አስመራ በመጨረሻም አዲስ አበባ ገቡ።

ትምህርታቸውን በፈረንሣይ ሀገር የተከታተሉት ደጃዝማች ግርማቸው ወደ ሀገራቸው ከመጡ በኋላ በስራው መስክ፣ በ1935 ዓ.ም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር፣ በስዊዲን የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ፣ በ1950 ዓ.ም ደግሞ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ፡ ከ1952 እስከ 1953 በምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኑ። የጐሬ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴም ሆነው ሰርተዋል።

ግርማቸው ተ/ሃዋርያት በድርሰቱ ዘርፍም በ1947 ዓ.ም አርአያ የተሰኘ ረጅም ልቦለድ ፅፈዋል። ይህ ልቦለድ በዘመኑ የት/ቤት የሥነ-ጽሑፍ ማስተማሪያ ሁሉ ሆኖ አገልግሏል። ዛሬም ድረስ የሥነ-ጽሑፉ ምሁራን እንደማጣቀሻ የሚጠቀሙበት መፅሐፍ ነው። ከዚሁ በመለጠቅም ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ ፅፈዋል። ስለ አፄ ቴዎድሮስ ማንነት እና ስብዕና ለመጀመሪያ ጊዜ የቴዎድሮስን አወንታዊ ጐን ላይ ተመርኩዞ የተፃፈ ቴአትር ነው። ከዚህ በተጨማሪም አድዋ የሚል ተውኔትም ፅፈዋል።

ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሃዋርያት በዘመነ ደርግ 8 ዓመታትን በእስር ተንገላተዋል። እስር ቤት እያሉ ህመም ስላስቸገራቸው ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር ሄዱ። ሞልቬር እንደፃፈው ከሆነ ጥቅምት 25 ቀን 1980 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው እኚህ የኢትዮጵያ ታላቅ ደራሲና ዲፕሎማት ማረፋቸውን ገልጿል።

በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተ/ማርያም

የደጃዝማች ግርማቸው አባት ናቸው። የተወለዱት እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም በአንኰበርና በደብረብርሃን መካከል ባላቸው መንደር ነው። የተማሩት ደግሞ ሩሲያ ነው። ውትድርናን እና ፈረንሣይ ደግሞ ጥበብን እንደተማሩ ይነገርላቸዋል። የእርሻም ትምህርት ተምረዋል። በጅሮንድ ተክለሃዋርያት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን ቴአትር ማለትም “ፋቡላ የአውሬዎች ኰሜዲያ” የተሰኘውን ተውኔት ፅፈው በ1913 ዓ.ም ለመድረክ አብቅተዋል።

በጅሮንድ ተክለሐዋርያት፣ በተማሩት የጦር ትምህርት ፋሽስቶችን ለመፋለም ስትራቴጂ ነድፈው ነበር። ከጃንሆይ ጋር ባለመግባባታቸው ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በኋላም በዚሁ ጦርነት ሳቢያ ወደ ጅቡቲ ተሰደዱ። ቀጥሎ ወደ ኤደን፣ ከዚያም ወደ ማዳጋስካር ተሰደው ኖረዋል። በነዚህ ግዜያትም ከውጭ ሆነው ለአርበኞች ልዩ ልዩ መዋጮዎችን፣ ወረጃዎችን እና ምስጢሮችን ይልኩ ነበር።

በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ተ/ማርያም የፃፉ የራሳቸውን የህይወት ታሪክ የሚያወሳ መፅሐፍም አላቸው። ኦቶባዮግራፊ (የህይወት ታሪክ) ይሰኛል። በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ኢትዮጵያን የገንዘብ ሚኒስቴር ሆነው አገለግለዋት ነበር። በ1969 ዓ.ም ሐረር ውስጥ ያረፉ ሲሆን ቀብራቸው የተፈፀመው ደግሞ ድሬዳዋ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን ነው።

ስንዱ ገብሩ

ስንዱ ገብሩ የደራሲነታቸውን ያህል የአርበኝነታቸው ታሪክም እጅግ ጐልቶ የሚታይ ነው። ጥር 6 ቀን 1907 ዓ.ም በአዲስ ዓለም ከተማ የተወለዱት ስንዱ ገብሩ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥ ሲከታተሉ ቆይተው ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ሲውዘርላንድ ሄድ ተምረዋል።

እኚህ ሴት አርበኛ እና ደራሲ፣ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር ወደ ጐሬ በመዝመት ከፍተኛ ተጋድሎ ፈፅመዋል። ልዩ ልዩ ቀስቃሽ ግጥሞችን እየፃፉ ለየ አውደ ውግያው ውስጥ ለሚሳተፉ አርበኞች ይልኩ ነበር። ለዚሁ ለሀገራቸው ነፃነት ሲዋደቁ በጠላት እጅ ወድቀው ተማረኩ። ከዚያም አዚናራ ተብሎ በሚጠራው የኢጣሊያ የባህር ወደብ ላይ ታሰሩ።

ከነፃነት በኋላም ደሴ በሚገኘው የወ/ሮ ስህን ት/ቤት ዳይሬክተር፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን የእቴጌ መነን የሴቶች ት/ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ዳይሬክተር ነበሩ። በፓርላማ ውስጥም የመጀመሪያዋ የሴት የፓርላማ አባል ሆነው ሰርተዋል።

ሰንዱ ገብሩ በ1942 ዓ.ም “የልቤ መፅሐፍ” የተሰኘና በብዙዎችም ዘንድ የተወደደ ስራቸውን አሳትመዋል። እጅግ በርካታ ያልታተሙ የልቦለድ፣ የግጥም እና የቴአትር ስራዎች አሏቸው። ቴአትሮቻቸው አብዛኛዎቹ ለመድረክ በቅተዋል። እነዚህም “አድዋ”፣ “የኢትዮጵያ ትግል”፣ “ከማይጨው መልስ”፣ “የታደለች ህልም” እና ሌሎችም በርካታ ስራዎች ይገኛሉ። ስንዱ ገብሩ የከንቲባ ገብሩ ልጅ ሲሆኑ እህታቸው እማሆይ ፅጌማርያም ገብሩ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ በእየሩሳሌም ገዳም ውስጥ በህይወት ያሉ ታላቅ የረቂቅ ሙዚቃ ሊቅ ናቸው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ

በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ደራሲዎች ከፋሽስቶች ጋር ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። እንደ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ ያሉ ታላላቅ ደራሲያንም በስደት ባሉበት ስፍራ ለምሳሌ ከእንግሊዝ ሀገር ሆነው ብዙ ለፍተዋል። የሀገራቸው በጠላት እጅ መውደቅ በጣሙን ያሳስባቸውና ያንገበግባቸው ነበር።

የኖርዌዩ ተወላጅ ሞልቬር ስለ ኅሩይ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል፤ ኅሩይ በወረራው ተጨንቀዋል። ይህ ወረራም መቼ አንደሚቀለበስ አያውቁትም፤ ይሄም አስጨንቋቸዋል።

(Hiruy was suffering mentally because of the Italian Occupation of Ethiopia, especially as he was not sure whether the country world never is free again.)

በጣም የሚያሳዝነው ግን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ ያረፉት ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እያለች መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ.ም ሉክሰንበርግ ውስጥ ነበር። ከነፃነት በኋላም በ1940 ዓ.ም አፅማቸው ከለንደን ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን አርፏል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ለምሳሌ እንደ መኰነን እንዳልካቸው፣ ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ፣ እና ሌሎችም የከፈሉት መስዋዕትነት እጅግ ግዙፍ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከጣሊያኖች ጋር ሆነው፣ ለኢጣሊያኖች ወግነው ብዙ የፃፉ የኢትዮጵያ ደራሲዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ በአፍሪካ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቦለድ የፃፈ እየተባለ የሚጠራው ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ (ዘብሔረ ዘጌ) ነው። ከርሱ በመለጠቅም ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም ለኢጣሊያኖች አግዘው ልዩ ልዩ መጣጥፎችን አቅርበዋል። ከበደ ሚካኤልም በጦርነቱ ወቅት ከኢጣሊያኖች ጋር ነበሩ። (እነዚህንና ሌሎችን ጨማምሬ በሌላ ጊዜ አጫውታችኋለሁ።)

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
15789 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1013 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us