የትዝታው ፈለግ አረፈ

Wednesday, 26 April 2017 12:16

 

በጥበቡ በለጠ

በኢትድጵያ የጽሁፍ ታሪክ፤ የመጣጥፍ፣ የአርቲክል ወይም ሃሣብን እና እምነትን ወግን፣ ባሕልን፣ ትዝታን ወዘተ በብዕር በመግለጽና፣ ውብ አድርጐ በመፃፍ አሰፋ ጫቦን የሚያክል ሰው ማግኝት ይከብዳል፡፡ ብዕሩ ወርቅ ነበር፡፡ ለዛ ያለው፡፡ አማርኛ ቋንቋ በአሰፋ ጫቦ ብዕር ውብ ናት፡፡ አቤት ገለፃ፤ አቤት ትረካ፤ አቤት የብዕር ጨዋታ፤ አቤት ትዝታ፤ አቤት ወግ፤ ይህን ሁሉ አጣን፡፡ ጋሽ አሰፋ ጫቦ አረፈ፡፡

ጋሽ አሴ፤ ምን ልበልህ? አረፍክ? ተለየኸን? ወይስ ሞትክ? ያ ብዕርህን የት ነው የማገኝው? ጋሽ አሴ የነፍስ ፀሐፊ ነበርክ፡፡

ኢትዮጵያ ሆይ፤ የጽሑፍ ጀግኖችሽን ፊት አውራሪዎችሽን ግለጪ ብትባል በመጀመሪያ ረድፍ  ላይ ስማቸው ተጠርተው ከሚቀመጡት መካከል ጋሽ አሰፋ ጫቦ አንዱ ነው፡፡

አሰፋ ጫቦ በትካዜ፣ በእንጉርጉሮ እና በትዝታ አለም ውስጥ ሆኖ የፃፋቸው መጣጥፎች ከይዘታቸው ባሻገር ቋንቋው ተአምር ነው፡፡ የሥነ-ጽሑፍ ብቃቱ የቃላቱ ሕብረ-ድምፅ፣ ኮሚክ ገለፃዎቹ ትረካዎቹ ወደር የሌለው ፀሐፊ ያሠኙታል፡፡ የአሰፋን ፅሁፍ ማንበብ ከጀመርን ረሐብ ይረሣል፣ ሌላ ነገር ማሠብ አይቻልም፡፡ ከጽሁፉ ጋር መጓዝ ከአሠፋ ጫቦ የትዝታ ፈለግ ጋር እየወጡ እየወረዱ መጓዝ  ብቻ፡፡  አሠፋ ጫቦ ሳናስበው ከዚያች ከትውልድ ቀኤው ጨንቻ ይወስደናል፡፡ ስለ ጨንቻ ጽፎ አይጠግብም፡፡ ጨንቻ የእርሡ ብቻ ሣትሆን የእኛም እንድትሆን አድርጓል፡፡

አሰፋ ጫቦ ታሪክ አዋቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የሕዝቦችዋን ቀደምት ታሪኮች ጠንቅቆ ያወቀ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ የሕዝቦችን ግኑኙነት ትስስር፣ ውጣ ውረድ በጥልቀት የተረዳ ነው፡፡ ይህ ታሪክ አዋቂነቱ ለሚጽፋቸው ርእሰ ጉዳዮች እንደ ሰበዝ እየተመዘዙ የሚያጫውቱ፣ እውነታን አስረግጠው የሚያስረዱ ናቸው፡፡

አሰፋ ጫቦ የሕዝብ ታሪክ ተንታኝ ነው፡፡ ይህች ኢትዮጵያ የምትባል አገር በውስጥዋ የያዘቻቸውን ሕዝቦች በታሪክ ሂደት ውስጥ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ በሚገባ ያወቀ እና የተረዳ በመሆኑ ይጽፍባቸዋል፡፡ ሲጽፍ ሕዝቦችን በፍቅር የሚያስተሣስር እንጂ የሚለያየ አይደለም፡፡ የሕዝቦች መተባበርና አንድነት የትልቋ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር መሆኑን የተረዳ ሠው በመሆኑ ሁሌም የፍቅር ፀሐፊ ነው፡፡

አሰፋ ጫቦ ተንታኝ ነው፡፡ እዚህም እዚያም የተበጫጨቁ ታሪኮችን ገጣጥሞ በመተንተን በቃላት ቤት ይሠራል፡፡ በቃላት መንደር ይሠራል፡፡ በቃላት ሀገር ይሠራል፡፡ በቃላት ኢትዮጵያዊነት ላይ ይገነባል፡፡

አሰፋ ጫቦ የቋንቋ ቱጃር ነው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ የመግለጽ ብቃት ከሚያሣዩ ፀሐፊያን መካከል አንዱ አሰፋ ጫቦ ነው፡፡ ውስብስብ ርዕሠ ጉዳዮችን ውብ በሆነ የአማርኛ ለዛ በመግለጽ የሚገዳደረው የለም፡፡ የአማርኛ ቋንቋ መፍቻ እና መገጣጠሚያ በእጃቸው ካሉ ፀሐፊያን መካከል አሰፋ ጫቦ ቶሎ ብሎ ከፊት የሚሠለፍ ነው፡፡

አሰፋ ጫቦ በኢትዮጵያ ፍቅር የተለከፈ ፀሐፊ ነው፡፡ ነጋ ጠባ ስለዚህችው ኢትዮጵያ ነው የሚጽፈው፡፡ የተነቃነቁ የታሪክ ክፍተቶችን ለመሙላት ብዙ ይጥራል፡፡ አሜሪካ ተኝቶ ሕልም የሚያየው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሕልሙ ትመጣለች፤ በሕልሙ ታሠቃየዋለች፡፡ በሕልሙ ይኖርባታል፡፡ በሕልሙ ያልምላታል፡፡ የአሰፋ ሕልም ኢትዮጵያ ነች፡፡ ሕልሙን በእውኑ ይጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና አሰፋ ሐይለኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ከአፈሯ ቢነጠልም ሁሌም ከትውልድ ቦታው ከጨንቻ አይጠፋም፡፡ በትዝታ ፈለግ ጨንቻ ነው፡፡

አሰፋ ጫቦ ሊቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እህህ ብላ አምጣ ከወለደቻቸው ሊቆች መካከል አንዱ አሰፋ ጫቦ ነው፡፡ በትምህርትና በስራ ልምድ በንባብና በጥናት ያካበተው የአሰፋ ጫቦ ጭንቅላት በብዙ መልኩ የተሟላ ነው፡፡ ከዚያ ከሞላው የእውቀት ማዕድ እየቆነጠረ ውብ በሆነው የአፃፃፍ ለዛው ሲመግበን የኖረ የዘመናችን ብርቅዬ ፀሐፊ ነበር፡፡

አሰፋ ጫቦ የፖለቲካ ሊቅ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ነው ካልኩት በአንድ የፖለቲካ አስተሣሠብ አጥር ውስጥ ይቀመጥብኛል፡፡ ለእኔ አሰፋ ፖለቲከኛ አይደለም፤ የፖለቲካ ሊቅ እና በብዕሩ የሚተነትናቸው ጉዳዮች ሰፊ እና ጥልቅ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ትንታኔው ማጠንጠኛ ሐረጉ የኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡ የትልቋ ኢትዮጵያ ምስል ነው፡፡ የአሰፋ ብዕር በተወሣሠበው የፖለቲካ ልዩነቶች ውስጥ ልዩ ልዩ ቅመሞችን በቃላት እያዘጋጀ ኢትዮጵያን አሻግረን እንድናይ የሚያደርግ የዘመናችን ቅን ብዕረኛ ነበር፡፡

አሰፋ ጫቦ ኮሚክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የብዕረኞች ታሪክ ውስጥ በፅሁፎቹ ለዛ እያሣቀን ዕንባ በዕንባ የሚያደርገን ሌላኛው ጳውሎስ ኞኞ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ሰው ፈረንጆቹ “ሂዩመሪስት” ይሉታል፡፡ እልም ባለ አሣዛኝ እና አስለቃሸ ታሪክ ውስጥ ከቶን ዝም አይልም፡፡ ከዚያ ሠቆቃ ውስጥ ቀስ ብሎ የሚያወጣን አስቂኝ ጉዳዮችን እያነሣ ነው፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡ አንዴ ታስለቅሳለች፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ታስቃለች፡፡ አሰፋ ጫቦ መራሩን ጣፋጩንም እያዋዛ አጥግቦ የሚያበላን የቃላት ባለሃብት የነበረ ብርቅ ፀሐፊ ነው፡፡

አሰፋ ጫቦ ድልድይ ነው፡፡ የአሰፋ ምድቡ ከዚያ ትውልድ ቢሆንም፣ሲያገለግል የኖረው አሁን እስካለው ትውልድ ድረስ ነው፡፡ ያለፈውን ታሪክ እያስታወሠ፣ አሁን ካለው ጋር እያስተሣሠረ፣ መጪዋን ኢትዮጵያ የሚያሣይ አሻጋሪ ፀሐፊ ነበር፡፡ በአሰፋ የብዕር ድልድይ ላይ ብዙ ታሪኮች አሉበት፡፡ ድልድዩ ብዙ ደም፣ ብዙ አጥንት የተከሠከሠበት ነው፡፡ ድልድዩ ግጭት አለበት፡፡ ድልድዩ ታሪክ አለት፡፡ ድልድዩ ሕዝብ አለበት፡፡ ይህ ድልድዩ ስደት አለበት፡፡ ድልድዩ መሰዋዕትነት አለት፡፡ ይህ የትውልድ ድልድይ እንዳይሠበር አሰፋ ብዙ ፅፏል፡፡ እናም አሰፋ ጫቦ የትውልድ ድልድይ ሠርቶ የሚያሻግር የዘመናችን ተወዳጅ ፀሐፊ ነበር፡፡

አሰፋ ጫቦ አለማቀፍ እውቀት ያካበተ ነው፡፡ አሰፋ በሚፅፋቸው መጣጥፎች ውስጥ ሃሣቦቹ ግዙፍ የሚሆኑለት በንባብ ያካበተው አለማቀፍ እውቀቱ ጥልቅ በመሆኑ ነው፡፡ ብዙ ማጣቀሻ ታሪኮች አሉት፡፡ የምድሪቱን ታሪክ ቆርጥሞ የበላ ሊቅ ነው፡፡ እናም በሚፅፋቸው መጣጥፎች ውስጥ የሃሣብ ቱጀር ነው፡፡ ብስሉንም ጥሬውን፣ጣፋጩንም ጐምዛዛውን፣ ሙቁንም ቀዝቃዛውን፣ ሀዘኑንም ሀሴቱንም ሁሉንም ነገር በውብ ቋንቋ መፃፍ የሚችል የዚህ ዘመን የተሟላ ፀሐፊ ነበር፡፡

ጋሽ አሴ፤ ስለ አንተ ስንቱ ይጠቀሣል? እኔስ ምን ልበል? አንድ ፅሁፍ ለመፃፍ ስነሣ ካንተ መጣጥፎች ውስጥ አንዱን መዘዘ አድርጌ ማንበብ አለብኝ፡፡ አንተ የመፃፍ መነቃቂያ ነህ፡፡ ሠው ውስጥ ያለውን የፅሁፍ ሆርሞን የምትቀሠቅስ ማትጊያ ቅመም ነህ፡፡ ምን ግዜም የማትረሳ የፀሐፊያን ብላቴን ጌታ ነህ! አንተ እንደምትኰምከው ሁሉ የቅርብህ ወዳጅህ፣ የእስር ቤት ጐደኛህ የሆነው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጁ ነብይ መኰንን ስለ አንተ መሰከረ፡፡  በደርግ ማዕከላዊ እስር ቤት ታስራችሁ በነበረበት ወቅት ያንተን ማንነት የሚያሣይ ምስክርነት አቀረበ፡፡ ነብይ ከዕንባው ጋር እየታገለ ስለ አንተ አወራ፡፡ ሲያወራ እያለቀስኩ ሣኩኝ፡፡ በለቅሶዬ ውስጥ አሣቀኝ፡፡ ጋሽ አሰፋ ማለት እንዲያ ነው፡፡ በለቅሶ ውስጥ የሚያስቅ፡፡ ነብይ መኰንን ስለ ጋሽ አሰፋ ጫቦ እንዲህ አለ፡-

ከአሰፋ ጫቦ ጋር አብረን ነበር የታሠርነው፡፡ እስር ቤት ሣለን ብዙ ነገሮች ያደርግ ነበር፡፡ ከነዚህም ውስጥ በኪሮሽ ሹራብ ይሠራ ነበር፡፡ በእጁ ሹራብ ይሠራል፡፡ አንድ ቀን እዚያ እስር ቤት አብረውን የነበሩ ታሣሪዎች ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት እለት ነበር፡፡  ለፍርድ ቤት መከራከሪያ እንዲሆናቸው አሰፋ ጫቦን ፃፍልን አሉት፡፡ እሺ አላቸው፡፡ ጉዳያቸውን ጠየቀ፡፡ አሰረዱት፡፡ ከዚያም ረጅም የፍርድ ቤት መከላከያ ደብዳቤ ፃፈላቸው፡፡ እነርሡም አመስግነውት ሄዱ፡፡ ፍ/ቤትም ደብዳቤውን አቀረቡ፡፡ ከዚያም ከፍርድ ቤት ሲመለሡ አሰፋ ጫቦ ሹራብ እየሠራ አገኙት፡፡ ገረማቸው፡፡ ያንን የመሠለ የሕግ ክርክር ደብዳቤ የፃፈላቸው ሊቅ እስር ቤት ውስጥ ሹራብ ይሠራል፡፡ እነዚህ እስረኞች እንዲህ ብለው ጠየቁት፡- አሴ አሁንም ይህን ሹራብ ትሠራለህ? አሉት፡፡ አሴም መለሰ፡- ሕግ ስለተማርኩ ዶርዜነቴ ይነጠቃል እንዴ? ዶርዜ እኮ ነኝ አላቸው፡፡

ነብይ መኰንን ሁለተኛውን ትዝታውን አወጋን፡፡

እዚያው እስር ቤት እያለን የማይፈቀዱ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ እስረኛ ምስማርና ስለት ያላቸውን ነገሮች ፈፅሞ ይዞ መገኘት የለበትም ይባላል፡፡ ምክንያቱም እስረኛው ራሡን በስለት እንዳያጠፋ ስለሚፈራ ነው፡፡ እንደየታሠረበት ሁኔታ ሚስጢር እንዳይወጣ እና ከምሠቃይ ራሴን ላጥፋ ብለው እስረኞች በራሣቸው ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ ስለት ነገር ተከልክሏል፡፡ ለአሠፋ ጫቦ ግን አንድ ደግ ፖሊስ አንዲት ቢላዋ ሠጥቶት ነበር፡፡ ብርቱካን ፍራፍሬ እየቆራረጠ እንዲበላበት ነበር የሠጠው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እስረኛው ዘንድ ቢላዋ ተገኘ፡፡ ወንጀል ስለሆነ ተጠራ፡፡ የተጠራው የእስር ቤቱ ሐላፊ ዘንድ ነበር፡፡ ሐላፊው ፈሪ ነው፡፡ ከላይ ያሉትን አለቆች ይፈራል፡፡ አሰፋ ጫቦ ደግሞ ደፋር ነው፡፡ አይፈራም፡፡ ፈሪ የእስር ቤት አዛዥ እና ደፋር እስረኛ ተገናኙ፡፡ የእስር ቤቱ አዛዥ አሰፋ ጫቦን እንዲህ ጠየቀው፡-

ቢላውን ለምን ያዝከው? ወንጀል መሆኑን አታውቅም? ይለዋል፡፡

አሰፋ እንዲህ መለሰ፡-

ምኑ ነው ወንጀል? ቢላዋ ብይዝ ምንድን ነው ችግሩ? ለማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሣል፡፡

የእስር ቤቱ አዛዥም በቢላዋው ራስህን ብታጠፋስ? ራስህን ብትገልስ? ይለዋል፡፡

አሰፋም እንዲህ መለሰ፡-

እኔ የምፈራው እናተ ትገሉኛላችሁ ብዬ እንጂ ጭራሽ እኔው ሆንኩ የምፈራው? አለ፡- ነብይ መኰንን፡፡ ከዕንባው ጋር እየታገለ አውግቶናል፡፡

አሰፋ ሜቦ የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርቱን ጨንቻ እና ሻሸመኔ፣ የሁለተኛ ደረጃ አዲስ አበባን (ኮከብ ጽባሕ) ተምሯል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወይም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ በመግባት በሕግ ትምህርት በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል፡፡ ገና በልጅነቱ ዓለማቀፍ ጉዳዮች ላይ ሀገሩን ወክሎ በመሔድ በዕወቀት አደባባይ ወደር የማይገኝለት ኢትዮጵያዊ ሆኖ የተመለሰ የቀለም ቀንድ ነበር፡፡

በስራው አለም ከብዙ በጥቂቱ በሕግ አማካሪነት፣ ሲቪል አቭዬሽን አስተዳደር፣ አገር አስተዳደር ሚኒስቴርና የምድር ባቡር ኩባንያ ውስጥ ሰርቷል፡፡ አውራጃ አስተዳዳሪም ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መስራች በመሆን በዘመነ ደርግም ሆነ በዘመነ ኢህአዴግ ተካፍሏል፡፡ በ1984 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለቆ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት አባልና በግሉም የሕግ ጠበቃ ነበር፡፡

አሰፋ ጫቦ ወደ ኢትዮጵያ የጽሑፍ አለም ውስጥ እንደ ክስተት ብቅ ያለው በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው፡፡ እርሱ እንደሚናገረው መጀመሪያ ለጋዜጦች የፃፍኩት በ1956 ዓ.ም ጎጃም ባህር ዳር እያለሁ “ፖሊስና እርምጃው” ላይ ነበር፡፡ አድሮ ውሎ “ፖሊስና እርግጫው” እንለው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ የባህር ዳርን ከተማ ለማስፋፋት በተጀመረ እቅድ ሳቢያ ኗሪ የነበረው ከቤቱ፣ ከቀዬው፣ ከርስቱ እየተነቀለ ሀብት ላለው ይታደል ስለነበር ያ ቆጥቁጦኝ የፃፍኩት ይመስለኛል፡፡ ርዕሱን አላስታውሰውም፡፡ “ጎጃሜው ተነቀለ!” የሚል ይመስለኛል፡፡ ምናልባት እርግጡ ያ ባይሆንም መንፈሱ ያ ነበር፡፡ ከአውራጃ ገዢውና ከማዘጋጃ ቤቱ ሹም ተግሳፅ ደርሶብኝ በዚያው አለፈ፡፡ ከዚያ ወዲህ አልፎ አልፎ ቢሆንም ብዙ የፃፍኩ ይመስለኛል” ይላል አሰፋ ጫቦ፡፡

አሰፋ ፃፈ አይባልም፡፡ አዘነበ ነው፡፡ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ሰጥቷል፡፡ አሰፋ የሓሳብ ሰው ነው፡፡ አሣቢ (Thinker) ነው፡፡ የሐሣብ ተጓዥ ነው፡፡ በሐሣብ ውስጥ የማያሳየን ዓለም የለም፡፡

አሰፋ ሲናገር ወጥቼ ቀረሁ ይላል፡፡ “ከ25 ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡ በ11 ያክል የአሜሪካ ግዛቶች ኖሬያለሁ፡፡ ያልኖኩባቸውን ወይ ነድቼ ወይም ከአየር አይቻለሁ፡፡ ያ ሁሉ ሆኖ ግን ህልም ባየሁ ቁጥር፣ ሰመመን ውስጥ በገባሁ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ መሬት፣ የኢትዮጵያዊያን ፊት ብቻ ነው የሚታየኝ፡፡ አንዳንዴ “አሜሪካ ነው ያልተቀበለኝ ወይስ እኔ ነኝ ያልተቀበልኩት?” በል በል ያሰኘኛል” ይላል ባለጣፋጭ ብዕሩ አሰፋ ጫቦ፡፡

አሰፋ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል፡፡ መለስ ብዬ ሳየው “ምነው ባላልኩት!” የምለው ብዙ አላገኘሁም፡፡ ሰፋ ቢል፣ የተሻለ ቢብራራ ኖሮ የምለው ብዙ አግኝቻለሁ፡፡ “በነጋታው ሲያዩት ቁልጭ ብሎ መታየት” የነበረ፣ ያለና የሚኖርም ነው፡፡ ሁሉም ላይ ባይሆን ጥቂቶች ላይ አንዳንድ ነጥቦች አነሳለሁ” ብሎ የትዝታ ፈለግ የተሰኘውን መፅሐፉን በሚከተለው መልኩ ያስተዋውቀናል፡፡

“ለመሆኑ ማነው ነፍጠኛ’ን አሁንም ለየት ባለ መልኩ አየዋለሁ፡፡ በግል ከማውቀው ከጋሙ ጎፋ፣ በተለይም ጨንቻና መንደርደሪያ አድርጊ የነፍጠኛን ማንነት ውስጡን ከፍቶ ለማየት ሙከራ ነበረ፡፡ በትግሬው ስሁል ሚካኤል የተጀመረው፣ ዘመነ መሣፍንት ተብሎ የሚታወቀው እስከ ቴዎድሮስ የነበረው አንድ መቶ ዓመት ኦሮሞ ኢትዮጵያን ያስተዳደረበት (የገዛበት) ዘመን ነበር፡፡ ኦሮሞው ግዛታቸው እስከ ሐማሴን ይደርስ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የነበረው መስፋፋት የምኒልክ ደቡብ ኢትዮጵያን መውረር ነበር፡፡ ይህ ኢትዮጵያን በብሔረሰብ ስብጥር፣ በባህል፣ በሐይማኖትና በሁለንተናው ፍፁም አዲስ መልክ የሰጠ ነው፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የዚህ (እና ከዚያ በፊት የነበሩ) ከፍተኛ የህዝቦች እንቅስቃሴ ውጤት ነች፡፡ ከእኔ የሚሻሉ ባሙያዎች ይህንን ውስጡን ከፍተው ቢያሳዩን በታሪክነቱ ብቻ ሳይሆን ዛሬ የሚታየውን አንዳንዴ የተዛባ የሚመስለውን የፖለቲካና የታሪክ ውይይትና ክርክር ደርዝና መሠረት ያለው ያደርገዋል የሚል እምነትም፣ ተስፋም ነበረኝ፡፡ አሁንም ሊጤንበት የሚገባው በአብዛኛው ክፍአት መስክ ይመስለኛል” በማለት ጋሽ አሰፋ ሃሳብ ይሰነዝራል፡፡ ይቀጥልና ይህን ይላል፡

“ኢትዮጵያን ይማሯት!” በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ የፃፍኩት ግልፅ ደብዳቤ ነው፡፡ በመጠኑ ታሪክን መሠረት አድርጎ በወቅቱ የነበረውን ሁናቴ የሚዳስስና መፍትሔ የሚመስል የሚጠቋቁም ደብዳቤ ነበር፡፡ የኤርትራን ጉዳይ፣ በተለይም በኤርትራና በትግራይ መካከል የነበረውን ታሪካዊ ቅራኔ የሚነካካ ነው፡፡ ደብዳቤው የተፃፈበት ዘመን ይርዘም እንጂ መሠረታዊ እውነቱ ዛሬም እዚያው ነው፡፡ ዛሬም ታላቂቱን ኢትዮጵያ የሚሹ፣ የሚያልሙ፣ ከአድማስ ባሻገር ማየት የሚፈልጉ፣ የሚችሉ፣ ልብ ሊሉት የሚገባው ነጥቦች እንደተጠበቁ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በወቅቱ የነበረው ገና “ነበረ” አልሆነም፡፡ ዛሬም “ነው” ነው፡፡ ይላል አሰፋ ጫቦ፡፡

“ትዝታ ነው የሚርበኝ” የግሌ የተወለድኩበት መንደር፣ ጨንቻን፣ የወጣሁበትን ጋሞን በወፍ በረር የሚዳስስ ነው፡፡ በተሳካ ሁኔታ ያየሁ/ ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ አንድ እንግሊዝ አገር የሚኖር ጓደኛዬ ኢትዮጵያ ደርሶ ሲመለስ፣ “ጨንቻም ሔጄ ነበር! አለኝ፡፡ “ምነው? በደህና? እዚያ ዘመድ አለህ እንዴ?” ስለው፣ “ምነው ከጨንቻ ነኝ አላልከንም እንዴ!” ብሎ ሣቁን ለቀቀው፡፡ ትዝታዬ ጎብኝም አስገኘ ማለት ነው፡፡ ስለ አካባቢያቸው፣ ስለ ት/ቤታቸው፣ ስለ መንደራቸው ማለት/መፃፍ ለሚፈልጉ የመጀመሪያ ረቂቅ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋሁ፡፡ ወረቀት ላይ የማስፈሩ ነገር እንጂ ትዝታ የማይበርደው ያለ አይመስለኝም”  ብል ፅፎልናል ጋሽ አሰፋ፡፡

“በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል” ማዕከላዊ እስር ቤት፣ ጨለማ ቤት ስለማውቀው ስለጎንደሬው ዶ/ር ካሳሁን መከተ ነው፡፡ ዶ/ር ካሣሁን ያኔም አሁንም ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ለየት ያለ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ማጥ ውስጥ ተዘፍቆ የገባበትን ማጥ አያውቅም ነበር፡፡ አንዳንዴ “ማወቅ አይፈልግም ነበር!?” የሚልም ይመጣብኛል፡፡ ዶ/ር ካሣሁን “እንደወጣ ቀረ!” ከሆኑት ብዙ ኢትዮጵያዊያን በጣም ከሚያሳዝኑኝ ውስጥ የሚደመር ነው” ሲል ጋሽ አሰፋ የትውልድ ቤተ-መዘክር እንደሆነ በፅሁፍ ያስታውሰናል፡፡

“እንዲህ መለስ ብለው ሲያዩት” ስለ ማዕከላዊ እስር ቤት ነው፡፡ እዚያ 10 ዓመት ከ6 ወር ከ6 ቀን ኖርኩኝ፡፡ መኖር ካልነው! በሕይወቴ አንድ ቤት ረዥሙን ጊዜ የኖኩት እዚያ ነበር፡፡ ይህ ወፍ በረር እንጂ ያንን ሲኦል በሙሉ የሚገልፅ አይደለም፡፡ በአንድ ሰውም፣ በአንድ ፅሁፍም፣ በአንድ መፅሐፍም ተነግሮ፣ ተወስቶ የሚያልቅ አይመስለኝም፡፡ ከደርግ ጋር የሚበቃው/ የሚያበቃ መስሎኝም ነበር፡፡ ብሶበት እንደቀጠለ ስሰማ ሁለንተናዬ ይደማል፡፡ በሌላ በትዝታዬ ወይም በሕይወት ታሪክ (Memoir) ወይም በደርግ ታሪክ እመለስበታሁ፡፡ ለዛሬው ይኸኛው በጨረፍታ ያሳይ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ” በማለት የትዝታ ፈለግ በተሰኘው መጽሐፉ መግቢያ ላይ ፅፏል፡፡

“የሞተ ተጎዳ” አድፍጠው ማጅራቴን መትተው ጥለው ለእስራት የወሰዱኝ ምሽት የሚያስታውስ ነው፡፡ መታሰሬ አይቀሬ መሆኑን ከተገነዘብኩ ሰንብቶ ነበር፡፡ ምን መልክ ይዞ እንደሚመጣ እርግኛ አልነበርኩም፡፡ የነበርኩበትን ፎቅ (Apartment) እንዳያሸብሩት አስቤ ማታ ማታ መዝጊያውን ሳልቆልፍ መተውም የጀመርኩ ይመስለኛል፡፡ ይኸኛው የሚቀጥው የአስር ዓመት ተኩል ጉዞዬ እንዴት እንደተጀመረ የሚገልጽ ነው፡፡ የፈሩት ባይደርስ ጥሩ ነበር ማለት ምኞት ነው፡፡

“የሞተ ተጎዳ” ያልኩት የኔን እድል ያላገኙ እንደወጡ የቀሩትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ለመዘከር ነው” ይላል ጋሽ አሴ፡፡ አፕሪል 23 ቀን 2017 አረፈ፡፡ በመጨረሻም እሱ ራሱ እንደወጣ ቀረ! ጋሽ አሴ ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኑራት!!!

/የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በአቶ አሰፋ ጫቦ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለፀ ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል/

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15714 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1019 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us