የባከነ ትውልድ

Wednesday, 19 April 2017 12:43


በጥበቡ በለጠ

 

ካመታት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ራስ ሆቴል አዳራሽ የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ጥበብን አፍቃሪያን በብዛት ታድመው ነበር። የታደሙበት ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ “ግጥምን በጃዝ” /Poetic Jazz/ የተሰኘውን መርሃ ግብር ለመከታተል ነበር። ከ700 ታዳሚ በላይ አዳራሹ ውስጥ ተገኝቷል። ያውም የመግቢያ ዋጋው ብቻ 50 ብር በሚከፈልበት የሥነ-ግጥም ዝግጅት! ሰው ተቀይሯል፤ ተለውጧል።


የሥነ-ግጥሙን ዝግጅት ያቀረቡት ከያኒያን ቀደም ሲል ታውቀዋል። እነርሱም ተፈሪ ዓለሙ፣ ነቢይ መኰንን፣ ግሩም ዘነበ፣ በኃይሉ ገ/እግዚአብሐር፣ ምንተስኖት ማሞ፣ ሲሳይ ጫንያለው፣ ዮሐንስ ገ/መድህን እና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው። ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ በኃይሉ ገብረእግዚአብሔር ወግ ሲያቀርብ፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ደግሞ “ግጥምና ፍልስፍና” ያላቸውን ተዛምዶ እና ተቃርኖን በተመለከተ ምሁራዊ ትንታኔ ሰጥተዋል።


ግጥምን በጃዝ /Poetic Jazz/ በተሰኘው በዚህ ዝግጅት ላይ ረጅሙን ጊዜ የወሰደው እና የአንድ ትውልድ ታሪክን የሚዳስሰው የሁለት ገጣሚያን ስራ ነው። የመጀመሪያው ገጣሚ ሽመልስ አማረ ይባላሉ። የሚኖሩት ከኢትዮጵያ ውጪ አሜሪካ ውስጥ ነው። የግጥም መጽሐፍ እና ሲዲ አሳትመዋል። አቶ ሽመልስ በዘመነ ወጣትነታታቸው የኢሕአፓ አባል ነበሩ። ያ የለውጥ አቀንቃኝ የነበረው ፓርቲ አያሌ ወጣት ኢትዮጵያዊያንን ያቀፈ ነበር። ሰፊ ትግል ጀመረ። አልተሳካለትም-ቀረ። ተበታተነ፣ በሃሳብ ተለያየ፣ ጫካ ገባ፣ ተዋጋ፣ አሁንም ተበታተነ። ሞተ፣ ተሰቃየ፣ ተሰደደ። እናም ከሞት ተርፎ በስደት ስላለው ስለዚያ ትውልድ ሽመልስ አማረ ረዘም ያለ ግጥም ጽፈዋል። ይህን ግጥማቸውን አርቲስት ግሩም ዘነበ በጥሩ የንባብ ለዛ አቀረበው።


የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ገጣሚ ነቢይ መኰንንም ለአቶ ሽመልስ አማረ ግጥም ምላሽ ጽፏል። የነቢይ ምላሽ ደግሞ የሚያተኩረው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለቀሩት የዚያ ትውልድ አባላት ነው። ነቢይ መኰንን ራሱ የዚያ ትውልድ አባል የነበረ እና ብዙ ነገር ያየ ገጣሚ ነው። በውጭ በስደት ስላለው እና በሀገር ውስጥ ስላለው የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ) የቀድሞው አባላት የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ሁለቱም ገጣሚያን በግጥሞቻቸው ሲገልፁ አመሹ። ተበትኖ ስለቀረው የኢሕአፓ ትውልድ ዘከሩ፣ አወሱ፣ ተቹ፣ አዘኑ…
ነቢይ መኰንን እና ሽመልስ አማረ የተቀባበሏቸው ግጥሞች ትኩረታቸው ያነጣጠረው “ያ ትውልድ” የድሮ ዓላማውን ትቶ፣ ዘንግቶ በተለያየ ዓለም ውስጥ መኖሩን ነበር። በውጭ ያሉት የድሮ የለውጥ አቀንቃኞች የድሮው ትግል ልክ አይደለም ብለው አንዱ ነጋዴ፣ አንዱ አስተማሪ፣ ሌላው ተማሪ፣ አንዱ ተላላኪ፣ አንድ የሌላ ፓርቲ አባል፣ አንዱ ሃይማኖተኛ፣ አንዱ ፀሐፊ፣ አንዱ ተራኪ ወዘተ እየሆኑ ዓላማቸው ተበትኗል ይላል ገጣሚ ሽመልስ አማረ። ነቢይ መኰንንም ይህን የሽመልስ አማረን አተራረክ መሰረት አድርጐ እዚህ ኢትዮጵያ ውሰጥ ስላሉት የዚያ ትውልድ አባላት የአሁን ይዞታ ያስቃኘናል።


እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት “የዚያ ትውልድ ታጋዮች” የሞቱለትን የደሙለትን፣ የቆሰሉበትን ትግላቸውን ትተው በሌላ መስመር ውሰጥ ናቸው። ግማሹ በጐሣ እና በሃይማኖት ተደራጅቷል። ግማሹ ሌላ ፓርቲ መስርቷል። ግማሹ “ኤሌክትሪክና ፖለቲካ በሩቁ” በሚል ትርክት ሁሉንም ነገር ትቶ በፍርሃት ዓለም ውስጥ ይዋኛል። አንዱ አድርባይ ሆኗል፣ አንዱ ተገልብጦ መጥቶ ተቃዋሚ ነኝ ይላል። ሌላውም እንዲሁ እያለ ኢሕአፓን ትቶታል! ያንን የትውልድ መዝሙር አያቀነቅንም!


የሁለቱ ገጣሚያን ስራዎች በይዘታቸው ተመሳሳይ ናቸው። ያ ትውልድ አንድ ሆኖ፣ የነፃነት መዝሙር ዘምሮ፣ ለውጥ እንዳላቀነቀነ ሁሉ ዛሬ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጐ እንደተወው ገጣሚያኑ ይተርካሉ። የኢሕአፓ የትግል መስመር ተለውጦ ታጋዮቹ ብትንተን ብለው ለምን ጠፉ?! የገጣሚዎቹ ብዕር ይህን አይናገርም። ኢሕአፓ ለምን ፈረሰ? መኢሶን ለምን ፈረሰ? እነ ነቢይ መኰንን ቀጣዩ ግጥማቸው በዚህ ዙሪያ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም “የዚያ ትውልድ ሕልም ለምን ጠፋ” የሚለው ጥያቄ ምርምርና ጥናትም በሰፊው ይጠይቃል።


ስለዚያ ትውልድ ማንነት እና ታሪክ ከፃፉ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ የኢሕአፓ መስራች እና ከፍተኛ የአመራር አባል የነበረ ነው። “ያ ትውልድ” በሚል ርዕስ ሦስት ትልልቅ ቅፅ ያላቸውን መፃሕፍት አሳትሟል። በእንገሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ “The Generation” በሚል እነዚህን ሦስት ቅጾች አሳትሟል። በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆይ የተሰኘተወዳጅ መጽሐፍ አሳትሟል። መጽሐፎቹ በተለይ ስለ ኢሕአፓ ፓርቲ አባላት፣ ማንነት፣ ስብስብ፣ ህልማቸውን፣ ትግላቸውን፣ ድላቸውን፣ ሽንፈታቸውን ወዘተ በዝርዝር ያሳያሉ።


ክፍሉ ታደሰ በነዚህ መፃህፍቶቹ የጓደኞቹን ህይወት ዘክሯል። የክፍሉ አፃፃፍ ለየት ያለ ነው። ቋንቋው ውብ ነው። ገለፃው ከመጽሐፍቶቹ ጋር አንባቢን በእጅጉ የሚያቆራኙ ናቸው። ሰውየው ከፖለቲካ አመራሩ በላይ በጣም የተዋጣለት ፀሐፊ ነው። ያንን ውስብስብ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቀላል ቋንቋ እና ግልፅ በሆነ የአፃፃፍ ትርክት ያሳየናል፤ ያሳትፈናል። ምናልባት ክፍሉ ራሱ የኢሕአፓ አመራር አካል በመሆኑ ለአፃፃፍ ስልቱ ውበት ምክንያት ሊሆን ይችላል። የአንድን ትውልድ ጅማሮ እና ፍፃሜ በሦስት መፃሕፍቶቹ በሚገባ አሳይቷል። በነገራችን ላይ የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ የተሰኙት ሦስት መፃህፍት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ኮፒ ከተሸጡ የኢትዮጵያ የታሪክ መፃሕፍት ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው። ክፍሉ በሕይወት ከተረፉት ሁለት የኢሕአፓ መስራቾችና አመራሮች መካከል አንዱ ነው።


እንደ ክፍሉ ታደሰ ሁሉ ያንን ትውልድ ከዘከሩ ፀሐፊያን መካከል አንዳርጋቸው አሰግድ ተጠቃሽ ነው። አንዳርጋቸው ባሳተመው መጽሐፍ “በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ…” በሚል ርዕስ የራሴ የሚላቸውን እነዚያን ተቀጣጥለው ያለቁ ትውልዶችን ዘክሯል። ይህ መጽሐፍ ርዕሱ ማራኪ ከመሆኑም በላይ በስልሳዎቹ ውስጥ ስለተነሱት ወጣቶች ከተፃፉት ሰነዶች መካከል በቋንቋውና በአተራረክ ውበቱ የሚጠቀስ ነው። መኢሶን እና ኢሕአፓ ተገዳድለው ያለቁ የዚህች አገር አሳዛኝ ትውልዶች ናቸው።


ያ የስልሳዎቹ ትውልድ እንደከፈለው መስዋዕትነት ያን ያህል የታሪክ መፃህፍትና የኪነ-ጥበብ ስራዎች አልተሰሩለትም። ግን በትንሹም ቢሆን የዓይን መስክሮች እየፃፉ ናቸው። የኢህአዴግ ሚኒስትር የነበሩት ሐርቃ ሐሮዬም በዘመነ ወጣትነታቸው ማለትም በቀይ ሸበር ወቅት የደረሰባቸውን፣ ያዩትን፣ የሰሙትን ታሪክ ጽፈው አሳትመዋል። የእርሳቸው መጽሐፍ በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ በዘመነ ኢሕአፓ የተከሰተውን አሳዛኝ እና አስከፊ ታሪክ ያስቃኘናል።


የኢሕአፓ ታጋይ የነበረውና በቅርቡ በህይወት ያጣነው አስማማው ኃይሉ ሁለት መፃህፍትን አበርክቷል። በተለይ ደግሞ በ2003 ዓ.ም ለንባብ ያበቃው ኢሕአሠ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት) የሚሰኘው መጽሐፉ በርካታ ጉዶችን ዘክዝኰ ያሳየበት ነው። ኢሕአሠ የኢሕአፓ የጦር ሠራዊት ክፍል ነው። በዚህ የጦር ሠራዊት ክፍል ውስጥ የነበሩ ችግሮች፣ ራዕዮች፣ ውድቀቶች እና ከሻዐቢያ እና ከሕወሓት ጋር የነበሩትን ግንኙነቶችና ተቃርኖዎችን በጥሩ ቋንቋ ተነባቢ አድርጐ አቅርቦታል። የኢሕአፓ ሠራዊት አሲምባ ተብሎ በሚታወቀው የትግራይ ግዛት ውስጥ እንዴት እንደተመቱ እና የውድቀታቸውንም ሁኔታ የዓይን ምስክር ሆኖ እና ነባር ታጋዮችን ጠይቆ መጽሐፍ አሳትሟል። የአስማማው ኃይሉ መጽሐፍ በውስጡ አያሌ ምስጢራዊ ሠነዶችን የያዘ የዚያ ትውልድ ማጣቀሻ ነው።


ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” እያለ የሚጠራው ኢሕአፓ ዛሬ አለ ወይ? ብለው የሚጠይቁ አሉ። በርግጥ የትውልዱ ርዝራዦች አሉ። ሲኖሩ ደግሞ እነ ገጣሚ ነቢይ መኰንን እንደገለፁት፤ የአይዲዮሎጂ መበታተን እና ከትግል መራቅን በዋናነት መለያቸው ሆኖ ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ዛሬም ድረስ የቀድሞውን የኢሕአፓ አስተሳሰብ የሚያራምዱ እና አጥባቂ ፖለቲከኞች አሉ። እንቅስቃሴያቸው ደግሞ ያን ያህል እዚህ ግባ የሚባልም አይደለም።


ኢሕአፓ እንደ ትግሉ ብዛትና የህይወት ውጣ ውረዱ መፃሕህፍትና ሌሎችም ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች አልቀረቡለትም። ክፍሉ ታደሰ በአራት ተከታታይ መጽሐፍቶቹ ስለ ኢሕአፓ ባይፅፍ ኖሮ የወጣቶቹ ታሪክ ምናልባትም አየር ላይ ተበትኖ ለትውልድ ሳይደርስ የሚቀር ነበር። ብዙ ተሳትፎ የነበራቸው የዚያ ትውልድ አባላት በወጣትነታቸው ያሳለፉትን የለውጥና የትግል ውሎ እምብዛም አልፃፉትም።


በሙዚቃው ረገድ ጭራሽ አልተሰራም። ከየቤቱ ወጣቶች ያለቁበትን የቀይ ሽብር ታሪክ የሚዘክሩ ሙዚቃዎች አልተሰሩም። ቴዲ አፍሮ በሰራው “ጃ ያስተሰርያል” በሚለው ዘፈኑ ጭራሽ ትግላቸውን ይኰንነዋል። ለለውጥ መነሳታቸው፣ አዲስ ስርዓት መፈለጋቸውን በአሉታዊ መልኩ ነው ያሳየው። ምናልባት ቴዲ አፍሮ የዚያን ትውልድ የመስዋዕትነት ጉዞ የተደራጀ መረጃ የለው ይሆናል። ምክንያቱም ቴዲ ራሱ የተወለደው በ1967 ዓ.ም ነው። ግን ደግሞ በጃንሆይ ዘመን ሳይወለድ ስለእርሳቸው ታላቅነት ዘፍኗል። ጃንሆይን ከፍ ለማድረግ የተማሪዎቹን ትግል እንደ ስህተት ቆጥሮታል። የኢሕአፓ መስራችና ከፍተኛ አመራር የነበረውና ዛሬም በህይወት ያለው ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ ብሎ ባሳተማቸው ጥራዞች ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በ1960ዎቹ የከፈሉትን ታላቅ መስዋዕትነት በሚገባ ይዘረዝራል። ቴዲ አፍሮ ደግሞ በተቃራኒው “አብዮት ብላችሁ…” እያለ ነቅፎአቸዋል። መስዋዕትነቱ እንደ ቴዲ አፍሮ ባለ ከያኒ በሚገባ ሊዘከር ይገባው ነበር። ለቴዲ አፍሮ “ያ ትውልድ” ምን ይሆን?


በፊልሙ ረገድም ስንመጣ ስለ ያ ትውልድ እምብዛም አልተሰራም። ግን አልፎ አልፎ ስራዎች ታይተዋል። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሣሌም መኩሪያ የመጀመሪያዋ ተጠቃሽ ናቸው። እርሳቸው በቀይ ሽብር ስላለቁት ወጣቶች የሁለት ሰዓት ተኩል ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው አሳይተዋል። የእርሳቸው ዶክመንተሪ አያሌ ምስሎችን የወሰደው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነበር። ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ወስደዋል። በተቻላቸው መጠንም የቀይ ሸብር ወቅት ሰቆቃን አሳይተዋል። እርሳቸው ራሳቸው በችግር ውስጥ ያለፉ እና ቤተሰባቸውም በወቅቱ በሞት ስለተቀጡ ከቁጭት ተነሳስተው የሰሩት ዶክመንተሪ ነው። ፕሮፌሰር ሳሌም ራሳቸው በአሜሪካን ሀገር የፊልም ትምህርት መምህርት ናቸው።


እንደ ፕሮፌሰር ሣሌም መኩሪያ ሁሉ ስለዚያ ትውልድ ፊልም የሰራው ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ በቀይ ሽብር ምክንያት ስላለቁት ወጣት ጓደኞቹ “ያልደረቀ ዕንባ” በሚል ርዕስ ፊልም አሰርቶ ፕሮዲዩስ አድርጐላቸዋል። ፊልሙ በእውነት ላይ የተመረኰዘ ፊቸር ፊልም ነው። በ1996 ዓ.ም የተሰራ ሲሆን በተለይ በውጭው ዓለም በተለያዩ ሀገሮች ታይቷል።


ቴዎድሮስ ተሾመ ደግሞ “ቀይ ስህተት” በሚል ርዕስ አንድ ፊቸር ፊልም ሠርቶ ነበር። ሙከራው ጥሩ ሆኖ ሳለ አያሌ የታሪክ ግድፈቶች አሉበት ተብሎም ሲተች ቆይቷል። ነገር ግን በቀይ ሽብር ዙሪያ ከተሰሩ ፊልሞች መካከልም ይመደባል።


የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ “ጤዛ” የተሰኘው ታዋቂ ፊልም በቀይ ሽብር ዙሪያ የተሰራ ነው። ኃይሌ ገሪማ በቀይ ሽብር ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖራቸው ሳቢያ ፊልሙን ከታሪክ አኳያ ጠንካራ ሊያደርጉት አልቻሉም እየተባሉ ይታማሉ። ነገር ግን ፊልማቸው ከቀረፃ ጥበብ እና ከድምፅ ቀረፃ አንፃር እጅግ የተዋጣለት ስራ መሆኑን ሁሉም ይስማማሉ። ከታሪክ ጭብጥ እና አፃፃፍ አንፃር ግን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንዳልሆነ የኢሕአፓን ታሪክ የሚተነትኑ ፀሐፊዎች ይገልፃሉ።


ወደ ስዕል ስራዎች ስንመጣ ቀድማ ብቅ የምትለው አስራ አንድ ዓመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የማቀቀችው ሰዓሊ እና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ ናት። እርሷ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን ሀገር የስዕል ጥበብ ታዋቂ መምህርት ስትሆን በስዕል ስራዎቿም እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች። በተለይ በቀይ ሽብር ወቅት ስለተገደሉት እና ስለተሰቃዩት ወጣት ጓደኞቿ “ዘ-ባር” እና “ሼክል” በተሰኙት ታላላቅ ስዕሎቿ የማስታወሻ ሐውልት አኑራላቸዋለች።


ከበደች ተክለአብ ከነክፍሉ ታደሰ ባልተናነሰ ሁኔታ ያንን ተቃጥሎ ተለብልቦ ስላለቀ ትውልድ ማስታወሻ አቅርባለች። በኢትዮጵያ የሥነ-ግጥም ታሪክ ውስጥ ወደር ከማይገኝላቸው ስራዎች ውስጥ የከበደች ተክለአብ ተጠቃሾች ናቸው። በ1980 ዓ.ም “የት ነው” በሚል ርዕስ ያሳተመችው የግጥም ስብስቦቿ የሰውን ልጅ የህይወት ውጣ ውረድ ከማሳየታቸው በላይ በቀይ ሽብር ምክንያት ከሀገሯ ኢትዮጵያ ተሰደው እና በሶማሊያ ጨካኝ ወታደሮች ተማርከው “መንዴራ” እና “ሃዋይ” በሚባሉ እስር ቤቶች ስላለቁት ጓደኞቿ ጽፋለች። እጅግ አሳዛኝ በሆኑት በእነዚህ ግጥሞቿ ከበደች በጣም የዳበረ እና የካበተ የስነ-ግጥም ተሰጥኦ ያላት ከያኒት መሆኗን ሃያሲያን ሁሉ ይስማሙበታል። ይህች ገጣሚት ለነዚያ በግፍ ስላለቁት ሰማዕታትና በእስር ተገማምደው ስለወደቁት ኢትዮጵያዊያን የግጥም ሀውልት አቁማላቸዋለች።


ያ ትውልድ እንደከፈለው መስዋዕትነት ያን ያህል ስራዎች አልተሰሩለትም። በተለይ በሙዚቃው ዘርፍ ምንም አልታየም ማለት ይቻላል። ሙዚቀኞቻችን በዚህ ዘርፍ ጥናት አድርገው ጥበባቸውን ቢያሳዩን መልካም ነው እላለሁ።


በቀይ ሽብር ዙሪያ ከፃፉ ሰዎች መካከል ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “Red Tears” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል። ደበበ እሸቱ “የደም ዕንባ” ብሎ ተርጉሞታል። ትርጉሙ ግን ችግር እንዳለበት አለምሰገድ ባስልዮስ በሰራው ከዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ጥናቱ ውስጥ አረጋጧል። ከዚህ በተጨማሪም ዛሬ በህይወት የሌሉት ታዋቂው የኢኰኖሚክስ ምሁር እሸቱ ጮሌም ስለዚያ ትውልድ ማንነት በሚጥም ቋንቋ ጽፈዋል። ሌሎችም ፀሐፊዎችን መጥቀስ ይቻላል። ግን ባክኖ ስለቀረው ያ ትውልድ በዚህች ገፅ ብቻ ጽፎ መጨረስ አይቻልም። እነ ነቢይ መኰንን በቆሰቆሱት የግጥም ዝግጅት ወደኋላ ሄደን ትውስታችንን እንቀጥላለን።

 

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15705 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1057 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us